
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የሆለታ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ወደስራ ያስገባቸው አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የኃይል አቅርቦትን በማሻሻል የላቀ ድርሻ እየተወጡ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለፁ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ጥላሁን አዘዘው እንደገለፁት ጣቢያው ለአካባቢው ማህበረሰብ እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለተሰማሩ በርካታ አምራች ድርጅቶች የተሟላ ኃይል በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡
የጥገና ባለሙያ ተዳቻ ገናሌ በበኩላቸው ጣቢያው የተገጠመለት ጂ አይ ኤስ መቆጣጠሪያ እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጣቢያው ኃይል ሳይቆራረጥ ደንበኞች ጋር ለማድረስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የኃይል መቋረጥ በሚከሰትበት ወቅት በቀላሉ ችግር የደረሰበትን መስመር እና የችግሩን ዓይነት እንዲሁም የችግሩን መጠን በመለየት የተሳካ፣ ፈጣንና ደህንነቱ የጠበቀ መፍትሔ ለመስጠት እንደረዳቸው ገልፀዋል።
የሆለታ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ500 ኪሎ ቮልት በደዴሳ በኩል በመቀበል ወደ 400 ኪሎ ቮልት ፤ለውጦ ለአቃቂ፣ ሰበታ እና ሱሉልታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች፣ ለደይሊ ውሃ እና ሀበሻ ሲሚንቶ ኃይል እያቀረበ ይገኛል።




