የደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ያልተቆራረጠ የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኘ መሆኑን አስታወቀ።
የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ የሺጥላ ሙሉጌታ እንደገለፁት ያልተቆራረጠ የኃይል አቅርቦት አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ለተጠቃሚው ለማቅረብ በእጅጉ አግዟቸዋል።

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኘው የሶላር ፓነል አምራች ኩባንያ በደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ ለመጀመር የቦታ መረጣ ማከናወኑን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ኩባንያው እስከ 40 ሜጋ ዋት ኃይል ሊጠቀም እንደሚችል ጠቁመዋል።
በቀጣይም በርካታ አምራች ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ ለመጀመር ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ገልፀው ለዚህም በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የደብረብርሃን ቁጥር 2 ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኜ ይታገሱ በበኩላቸው ጣቢያው 33 እና 15 ኪሎ ቮልት አቅም ባላቸው 15 ወጪ መስመሮች ለኢንዱስትሪዎች፣ ለደብረብርሀን እና በዙሪያው ለሚገኙ ወረዳዎች በአጠቃላይ በቀን እስከ 140 ሜጋ ዋት ኃይል በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ዳኜ ገለፃ ጣቢያው ከሚጭነው 140 ሜጋ ዋት ውስጥ በ230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር አማካኝነት ለለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀን 50 ሜጋ ዋት ኃይል በማቅረብ ላይ ነው።
የካቲት 2011 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ ጣቢያ የኃይል አቅርቦቱን የሚያሳልጡ ሁለት አውቶ ትራንስፎርመሮች እና ሁለት ፓወር ትራንስፎርመሮች አሉት።


