ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስከበረ እና ሀገራዊ አንድነትን ያጠናከረ ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክት መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገለፁ።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለፁት ግድቡ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ መሥራትና ማሳካት እንደሚችሉ ለመላው ዓለም ያረጋገጡበት ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው።
የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ መግባቱ የሀገሪቱን የኃይል ማመንጨት አቅም በእጥፍ እንዳሳደገው ተናግረዋል።
ከህዳሴ ግድብ በፊት ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የጊቤ 3 እና የበለስ እንዲሁም ሌሎች የኃይል ማመንጫዎች በጥቅል የሚያመነጩት ኤሌክትሪክ ህዳሴ ግድብ ከሚያመነጨው 50 በመቶ ያህሉን ብቻ የሚሸፍኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ይህም ግድቡ በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ዘርፍ ላይ ከፍተኛ እመርታ ያመጣ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በሀገሪቱ ከተመረተው ከ33 ሺህ ጊጋዋት ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 52 በመቶ የሚሆነው ከዚሁ ግድብ የመነጨ ነው።
ይህ ከግድቡ የመነጨው ከፍተኛ የኃይል ምርት ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችና ማህበራዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከቱን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ለውጭ ሀገራት ለሚደረገው የኃይል ሽያጭ ዕድገትም አስተማማኝ መሰረት መጣሉንም ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት ተቋሙ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 124 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ እና 39 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ጠቅሰው ለዚህም ስኬት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የ52 በመቶ የኃይል ምርት ድርሻ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከቱን አስረድተዋል።