የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በደሴ ከተማ እያስገነባ የሚገኘውን የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን በተቋሙ የኢንጂነሪንግ እና ኮንስትራክሽን ዘርፍ አስታወቀ።
በዘርፉ የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ከፈለኝ እንደገለፁት ተቋሙ ለስድስት አቅመ ደካማ አባወራዎች መኖሪያ የሚውል ባለ አንድ ፎቅ (ጂ+1) ህንፃ በ28 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ እያስገነባ ይገኛል።


መጋቢት 15 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረውን የቤት ግንባታ የመሠረት ሥራ በማጠናቀቅ ኮለኖችን የማቆም ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በግንባታው ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ወቅታዊ የነዳጅ እጥረት የግንባታ ግብአቶችን ለማጓጓዝ ተግዳሮት የፈጠረ መሆኑን የገለፁት አቶ ቴዎድሮስ የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎችን በመውሰድ እስከ በጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ድረስ ቤቶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ተቋሙ ከተሰጠው ተልዕኮ ባሻገር በመላ ሀገሪቱ የማህበራዊ አገልግሎት ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

