ያለ ተፈጥሮ ወንዝና ግድብ ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሙከራ፤

ያለ ተፈጥሮ ወንዝና ግድብ ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሙከራ፤

አንድ አሜሪካዊ ያለ ተፈጥሯዊ ወንዝ ወይም ግድብ የሚሰራ “ዝግ-ሉፕ” የተሰኘ የውሃ ኃይል ማመንጫን ሙከራ አድርጓል፡፡

ማመንጫው ተፈጥሯዊ ወንዝ ወይም ግድብ የሌለው ሲሆን የመሬት ስበትን፣ ከፍታን እና ጥቅም ላይ የዋለ ውሃን በመጠቀም በደረቃማና ግድብ በሌላቸው አካባቢዎች ጭምር የማያቋርጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ነው።

ይህ ግኝት ከአሁን ቀደም የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ያልነበሩ አካባቢዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

ማመንጫው በቀን ውስጥ የፀሐይ ኃይልን ወይም የንፋስ ኃይልን በመጠቀም ውሃን ወደ ከፍተኛ ከፍታ ማጠራቀሚያ ቦታ በመውሰድ የሚሰራ ሲሆን ከፍተኛ ፍላጎት በሚኖርበት ወይም ፀሐይ በምትጠልቅበት ስዓት ደግሞ ውሃውን ወደ ታች በተርባይኖች በመልቀቅ እንደ ውሃ ኃይል ማመንጫዎች ኤሌክትሪክ ያመነጫል።

ከዚያም ውሃው በታችኛው የተፋሰስ ቦታ ላይ ተሰብስቦ በፓምፖች አማካኝነት እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችል ሲሆን ኃይልን እንደ ባትሪ ማከማቸት እና ለግሪድ ፍላጎቶች ወዲያውኑ ምላሽ ለመስጠትም የሚረዳ ነው ተብሏል።

ይህ ግኝት ብዙውን ጊዜ የጎርፍ አደጋን ከሚያስከትሉ፣ ነዋሪዎችን እና የዱር እንስሳትን ከሚያፈናቅሉ ግድቦች በተቃራኒ የአካባቢ ተጽዕኖ የሌለው፣ የተፈጥሮ ወንዞችን አቅጣጫ የማያስቀይር፣ በዓሳን ሀብት የተሰማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የማይጎዳ እና ግዙፍ የግንባታ ሥራዎችን የማይፈልግ ነው።

በተጨማሪም ማመንጫው በረሃን ጨምሮ ጥቅም ላይ ባልዋለ መሬት እና አነስተኛ የነዋሪ ቁጥር ባላቸው ቦታዎች በመገንባት በአካባቢው ያለውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ያስችላል።

ያለ ተፈጥሮ ወንዝና ግድብ ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሙከራው በአሜሪካ በአሪዞና እና ኔቫዳ ግዛቶች ተሞክሮ ከ80 በመቶ በላይ ውጤታማ በመሆን ከሊቲየም ባትሪዎች እኩል አቅም እንዳለው ተረጋግጧል።

ግኝቱ ግዙፍ የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታ ሳይፈልግ እና ጥቅም ላይ የዋለ ውሃን በመጠቀም ታዳሽ ኢነርጅን ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top