የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሰዓትም ሆነ ቀን አይመርጥም። በመሆኑም የዘርፉ ባለሙያዎች በበዓላት፣ በሳምንት መጨረሻዎች፣ በሌሊት እንዲሁም በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ ሳይበገሩ በ24/7 የፈረቃ ሥራና በተጠንቀቅ ዝግጁ ሆነው አገልግሎት ይሰጣሉ። ይህ ጥረት ተራ የሥራ ግዴታ ሳይሆን ግላዊ፣ ማህበራዊና ቤተሰባዊ ሕይወታቸውን ከሀገራዊ ጥሪ ጋር አጣጥመው የሚያገለግሉበት የላቀ የመስዋዕትነት ማሳያ ነው።
የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያዎች ጥገና ቀላል ተግባር አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሰከንድ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅና ከሕይወት አደጋ ጋር የሚደረግ ቀጥተኛ ፍልሚያ ነው።
ባለሙያዎቹ በአስቸጋሪ መልከዓ-ምድር ውስጥ በሚገኙ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ በመውጣት ከፍተኛ ቮልቴጅ በሚያልፍባቸው የማስተላለፊያ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ ይሰራሉ። ትንሿ ስህተት ውድ የሕይወት ዋጋ ልታስከፍል እንደምትችል እያወቁ ፍርሃትን በጽናት ተክተው ሥራቸውን ያከናውናሉ።
በተፈጥሮ አደጋ፣ በመብረቅ ምት ወይም በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት የኃይል መቋረጥ ሲከሰትም እነዚህ የብርሃን አምባሳደሮች ሰከንድ ሳይሰስቱ ወደ ጥገና ሥራ ይሰማራሉ። አደጋው የደቀነውን ፈተና በሙያዊ ብቃት በመጋፈጥ የተቋረጠውን ኃይል በፍጥነት ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያደርጉት ርብርብ የላቀ የሕዝብና የሀገር ፍቅር ማሳያ ነው።
በዚህ «የፅናት ቀን» ለህዝባችን ብርሃንና ለሀገራችን ኢኮኖሚ ማንሰራራት ሲሉ 24/7 መስዋዕትነት ለሚከፍሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎች በሙሉ ኩራታችንንና አክብሮታችንን እንገልጻለን! 🇪🇹✨
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”