የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዋና መስሪያ ቤት ዘመናዊ የመካከለኛ ጋራዥ ግንባታ ለማከናወን የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጋር በስካይ ላይት ሆቴል ተፈራረመ።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ኮሎኔል ሸጋው ጌታ ናቸው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት የጋራዥ ግንባታ ሥምምነቱ ተቋማቱ በቀጣይ በትብብር አብረው ለመስራት የሚያስችል መሰረት የሚጥል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚገነባቸው ከፍተኛ የኃይል መሰረተ ልማት ግብዓቶችን በአብዛኛው ከውጭ ሀገር የሚያስገባ መሆኑን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኢንጂነሪንግ ግሩፑ ወደፊት የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ የብረት ምሰሶዎችን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን በጥራት በማምረት ለተቋሙ ለማቅረብ መስራት እንደሚገባው አብራርተዋል፡፡
ይህም ከውጭ የሚገባን ግብዓት በሀገር ውስጥ በመተካት ጊዜንና ወጪን በመቆጠብ መንግሥት የያዘውን የኢትዮጵያ ታምርት ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይ የሀገር ውስጥ አቅምን አስተባብሮ ውጤት ለማስመዝገብ ተቋሙ ከመሰል ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ኮሎኔል ሸጋው ጌታ የመካከለኛ ጋራዥ ግንባታው በግሩፑ የብረታ ብረት ማምረቻ ኢንዱስትሪ በኩል የሚከናወን ሲሆን በአጭር ጊዜ በጥራት አጠናቆና ዕቃዎቹን አሟልቶ ለማስረከብ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ኢንጂነሪንግ ግሩፑ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በግብዓት አቅርቦት እና በተለያዩ ዘርፎች ትብብሩን አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ በበኩላቸው ተቋሙ በመላ ሀገሪቱ ግዙፍ የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችንና የኦፕሬሽን ሥራዎችን የሚያከናወን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለሥራው የሚያስፈልጉ ከአንድ ሺህ በላይ ተሸከርካሪዎች አሉት፡፡

የተሽከርካሪዎቹ ጥገና በውጭ ጋራዥ መከናወኑ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣና ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በተቋሙ የፕሮጀክትና የኦፕሬሽን እንቅስቃሴዎች ላይ እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ተቋሙ የራሱን ዘመናዊ መካከለኛ ጋራዥ በመገንባት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍና ሥራዎችን ለማሳለጥ ስምምነቱ መፈረሙን ገልጸዋል፡፡
ሥምምነቱ ጋራዡን በመገንባትና ዕቃዎቹን በማሟላት ለአገልግሎት ዝግጁ እስከማድረግ የሚጠቃልል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደመረ ለዚህም ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙንም ተናግረዋል፡፡
ዘመናዊ ጋራዡን በተያዘለት የጊዜ ገደብ አጠናቆ ወደ አገልግሎት ለማስገባት አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡




