ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ የሥራ መሪዎች “በሥነ-ምግባርዊ የውሳኔ አሰጣጥና በጥቅም ግጭት መከላከል” ዙሪያ የተሰጠው ስልጠና ተጠናቋል።
ሥልጠናው የተቋሙን የአሰራር ሥርዓት በዘመናዊና ግልጽነት በተሞላበት መንገድ ለመምራት፣ የጥቅም ግጭቶችን ለመከላከል እና ለተቋሙ ተልዕኮ መሳካት ወሳኝ የሆኑ መሠረቶችን ለመጣል ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንደገለጹት ስልጠናው አመራሩ በተለያዩ ጉዳዮች የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች ሥነ- ምግባር በተላበሰ መልኩ እንዲፈጽም ለማድረግ እና ከጥቅም ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ቀድሞ ለመከላከል ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡
የኮርፖሬት ፋይናንስና ኃብት አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አሰፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ በበኩላቸው ስልጠናው በተቋሙ የጥቅም ግጭት ያለባቸው የስጋት አካባቢዎችን በመለየትና የመከላከያ ስልቶችን በመተግበር የተሻለ ተቋም ለመገንባት ያግዛል ብለዋል፡፡
የሥነ- ምግባርና ፀረ- ሙስና መከታተያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አጥናፌ እንደተናገሩት ስልጠናው አመራሩ ሥራውን በራስ የመተማመኑ ሁኔታ ተጠብቆ እንዲሰራ እና ወደፊት ከሚከሰቱ አሉታዊ ተጽእኖዎች ራሱን እንዲጠብቅ ለማስቻል በግብዓትነት ያገለግላል፡፡
ከሥልጠናው ዋና ዋና ነጥቦች፦
✅ ስርአትን ማጠናከር፦ ውሳኔዎች በግለሰብ ስሜት ሳይሆን በተቋቋመው ሥርዓት (System) እንዲመሩ በማድረግ ግልጽነትን ማስፈን፤
✅ ቅድመ-መከላከል፦ የጥቅም ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ የስጋት ቀጠናዎችን በመለየትና በመቆጣጠር ብልሹ አሰራርን መከላከል፤ ይህንን ሥራ በፖሊሲ ለማስደገፍ ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለምስክርነት ቀርቧል።
✅ ዓለም አቀፍ ደረጃ፦ ተቋሙ በፀረ-ሙስና አስተዳደር ሥርዓት (ISO 37001) ሰርተፊኬት እንዲያገኝ እየተደረገ ያለውን ጥረት በማፋጠን ተወዳዳሪና ታማኝ ተቋም መገንባት።
✅ ወጥነትና ተጠያቂነት፦ አመራሩ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች በሥነ-ምግባር መርሆዎች ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ለሠራተኛውም አርአያ የሚሆን የአመራርነት ስሜት መፍጠር።
የተቋሙ የሥራ መሪዎች ስልጠናው የንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን ወደ ተግባር የሚቀየር፣ ክትትልና ግምገማ የሚደረግበት፣ እንዲሁም ወደታችኛው የሥራ ክፍል የሚወርድ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ጥራት ያለው የኃይል አቅርቦትን ለሀገራችን ለማድረስ ስንሰራ፣ በሥነ-ምግባር የታነጸና ብልሹ አሰራርን የሚፀየፍ የሰው ኃይል መገንባት የጉዟችን አካል ነው።



