ከሚያዚያ 30 በፊት ሀብታቸውን ያላስመዘግቡ የተቋሙ ሠራተኞች ቅጣት ይጠብቃቸዋል

ከሚያዚያ 30 በፊት ሀብታቸውን ያላስመዘግቡ የተቋሙ ሠራተኞች ቅጣት ይጠብቃቸዋል


‎እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የተቋሙ ሠራተኞች ለቅጣት የሚዳረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታትያ መምሪያ ገለጸ።
‎
‎በመምሪያው የሙስና ተጋላጭነትና ሥልጠና ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግሥቱ አባይነህ እንደገለጹት በሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች ሀብታቸውን የማስመዝገብ ግዴታ አለባቸው።
‎
‎ሠራተኛው የራሱን እና የትዳር ጓደኛውን እንዲሁም ከ18 ዓመት በታች የሆነ ልጁን ጨምሮ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት፣ የገቢ ምንጭና ዕዳ ማስመዝገብ ይኖርበታል ብለዋል።
‎
‎ሆኖም በውርስ የተገኘ የጋራ ንብረት፣ የቤት ዕቃዎች፣ የግል መገልገያዎችና የጡረታ ገቢ በአዋጁ ከምዝገባ ነጻ መሆናቸውን አብራርተዋል።
‎
‎አዋጁን መሠረት በማድረግ ሁሉም ሠራተኛ ማስመዝገብ ያለበት ቢሆንም መምሪያው ለአሠራር እንዲያመች በተቋሙ ከPR 1 የሥራ መደብ በላይ ያሉ ሠራተኞች ሀብታቸውን እስከ ሚያዚያ 30 ቀን እንዲያስመዘግቡ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
‎
‎ምዝገባው የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር በበለፀገው ሶፍትዌር የሚከናወን በመሆኑ መምሪያው እስከ አሁን ከ1 ሺህ 243 ሠራተኞች ውስጥ 982 ሠራተኞችን ከሲስተሙ ጋር የማገናኘት ሥራ ማከናወኑን ጠቁመዋል።
‎
‎ሆኖም እስከ አሁን በሲስተሙ ገብተው ሀብታቸውን አስመዝግበው ሠርተፍኬት የወሠዱ ሠራተኞች 304 ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል።
‎
የተቋሙ ሠራተኞች ከሚያዘያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በፊት ምዝገባውን ካላከናወኑ በኮሚሽኑ አንድ ሺህ ብር ተቀጥተው ሀብታቸውን እስከሚያስመዘግቡ ድረስ ደመወዛቸው እንደሚታገድ አብራርተዋል።
‎
‎የሀብት ምዝገባው ላይ የሚኖረው ተሳትፎ በተቋሙ ገጽታ ላይ አስተዋጽኦ እንዳለው በመረዳት በቀሪ ጊዜያት ሁሉም የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

Scroll to Top