ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የኃይል ምንጭ በአግባቡ የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን አስጠብቃ ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆኗን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ እንደገለፁት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራስ አቅም መገንባቱ የሀገሪቱን ጽናትና ጀምሮ የመጨረስ አቅም በተግባር ያረጋገጠ ታላቅ ምዕራፍ ነው።
የግድቡ ግንባታ እና የውሃ ሙሌት ሂደት የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድር መጠናቀቁ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ይነሱ የነበሩ ስጋቶች ፍጹም መሰረተ ቢስ መሆናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል።
ሀገሪቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከማጠናቀቅ ባሻገር የቀድሞ ጥናቶችን በመከለስ እና አስፈላጊውን ፋይናንስ በማሟላት ተጨማሪ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል።
ማንም አካል ኢትዮጵያን ከጀመረችው የልማት ጉዞ ሊያስቆማት እንደማይችል ዋና ሥራ አስፈፃሚው አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አክብራ፣ ከምታመነጨው ንጹህ የኤሌክትሪክ ኃይል አፍሪካውያን እንዲቋደሱ እያደረገች የማንሰራራት ጉዞዋን በስኬት ታስቀጥላለች ብለዋል።