የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2018 በጀት ዓመት ያለፉት ዘጠኝ ወራት ከ27 ሺህ በላይ ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል መመረቱን አስታወቀ።
የኮርፖሬት ፕላኒግ ተወካይ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያለውአይቀር ማንደፍሮ የተቋሙን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 29 ሺህ 381 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ሰዓት ለማምረት ታቅዶ 27 ሺህ 105 ነጥብ 6 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማምረት ተችሏል።



ይህም የዕቅዱ 92 ነጥብ 4 በመቶ መሳካቱን የሚያሳይ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመረተው ኃይል የ27 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከመነጨው ኃይል ውስጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ 50 ነጥብ 8 በመቶ እንዲሁም የጊቤ ሦስትና የበለስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የ18 ነጥብ 3 በመቶ እና የ6 ነጥብ 9 በመቶ በማመንጨት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው ተጠቅሷል።
በበጀት ዓመቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ጨምሮ የአይሻና የአሰላ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ኦፕሬሽን በመግባታቸው የማመንጨት አፈጻጸሙ የተሻለ እንዲሆን ማድረጉን ጠቅሰዋል።


የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ጠንካራና ቀጣይነት ያላቸው የጥገና ሥራዎች ሲከናወኑ እንዲሁም በማዕቀፍ ግዥ ጭምር የመለዋወጫ ዕቃዎች ሲቀርቡ መቆየታቸውን አንስተዋል።
በቀሪ ሦስት ወራት የግድቦችን ደህንነት በማረጋገጥ እና የነበሩ ክፍተቶችን በማረም እንዲሁም አማካይ የኃይል ጭነትን በማሻሻል የታቀደውን ዓመታዊ የኃይል ምርት ግብ ለማሳካት እንደሚሰራ አቶ ያለው አይቀር ተናግረዋል::
ከመነጨው ኃይል ውስጥ 24 ሺህ 970 ጊጋ ዋት ስዓት ኃይል መሸጡንም ጠቁመዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


