በተቋሙ የጥቅም ግጭት ስጋቶችን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን በትኩረት ይሰራል

በተቋሙ የጥቅም ግጭት ስጋቶችን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን በትኩረት ይሰራል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጥቅም ግጭት ስጋቶችን ለመከላከል እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት እንደሚሰራ ተገለፀ፡፡

“ሥነ – ምግባራዊ የውሳኔ አሰጣጥና የጥቅም ግጭት መከላከልና ማስተዳደር” በሚል ርዕስ ለተቋሙ ከፍተኛ የሥራ መሪዎች ስልጠና የሰጡት በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የድህረ- ምረቃ ፕሮግራሞች አስተባባሪ አወቀ አሸናፊ (ዶ/ር ) በሥነ ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶችና መርሆዎች፣ የጥቅም ግጭት ምንነት፣ አይነቶች፣ መንስኤዎች፣ ተጋላጭነትና ስጋቶች እንዲሁም መከላከያ ስልቶችና ማስተዳደሪያዎች ላይ ገለፃ አድርገዋል።

በገለፃቸውም በተቋሙ ከፕሮጀክት ትግበራ፣ ከተቋማዊ አደረጃጀት፣ ከግዥ ሂደቶች፣ ከካሳ ክፍያ አሰራር፣ ከንብረት አስተዳደርና አወጋገድ፣ ከኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ሥራዎች እንዲሁም ከተቋሙ የሰው ሃብት ልማትና አስተዳደር ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለጥቅም ግጭት አጋላጭ የሆኑ ስጋቶች መኖራቸውን አስረድተዋል።

በሥልጠናው ላይ የተሳተፉት የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች ተጠያቂነትን ከማስፈን፣ ከአደረጃጀት፣ ከንብረት አስተዳደር፣ ከተቋማዊ የቁጥጥር ሥርዓት፣ ከግዥ ሂደትና ከባለሙያዎች አቅም ግንባታ እንዲሁም በስልጠናው ላይ በተነሱና መስተካከል ይገባቸዋል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች፣ አስተያየትና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

የጥቅም ግጭት ስጋት ተብለው ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ የተነሱት ጉዳዮች የተቋሙን ወቅታዊ ቁመና የማያሳዩ መሆናቸውን የሥራ ኃላፊዎቹ የተለያዩ ማሳያዎችን በመጥቀስ አስረድተዋል።

በተቋሙ ተግባራዊ የተደረገው አደረጃጀት የሥራ መደራረብን ለማስቀረት፣ በተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ላይ የነበሩ ጫናዎችን ለማቃለልና ሀብትን በአግባቡ ለማስተዳደር የተቀረጸ እንጂ ሰዎችን ለመጥቀም ታስቦ የተዘጋጀ ባለመሆኑ አደረጃጀቱ ያመጣው ለውጥና የፈጠረው ችግር ካለ መገምገም እንደሚገባው የሥራ ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል።

የንብረት አስተዳደርን በተመለከተም አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን የማስወገዱ ሥራ በሀገር ደረጃ ያለውን የግዥና ንብረት ማስወገድ አዋጁንና ይህን ተከትሎ በተቋሙ የተዘጋጀውን መመሪያ መሠረት በማድረግ እየተከናወነ ስለመሆኑ ተገልጿል።

አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች በተለያዩ ኮሚቴዎች አማካኝነት ተለይተውና ተረጋግጠው የጨረታ ሂደቱ በሦስተኛ ወገን በኦንላይን የጨረታ ሥርዓት ከጥቅም ግጭት በፀዳ መልኩ እየተፈፀመ እንደሆነ ተነስቷል፡፡

በተቋሙ የኮርፖሬት ገቨርናንስና ኮምፕሊያንስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዱጉማ ነዳ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ እንደተናገሩት ተቋሙ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን ሚናና የተሰጠውን ተልዕኮ ታሳቢ በማድረግ ለጥቅም ግጭት ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎችን በጥናት የመለየት ሥራ ተሰርቷል፡፡

በተቋሙ የጥቅም ግጭት ስጋቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን በቀጣይ የሕግ ማዕቀፎችን በመከለስ፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

የሥራ መሪዎች ውሳኔዎችን ሥነ – ምግባርን በተላበሰ መንገድ በመስጠት እንዲሁም የመተዳደሪያ ደንቦችን እና የአሰሪና ሠራተኛ ስምምነት ድንጋጌዎችን በማክበር ለተቋማዊ ስኬት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

Scroll to Top