ሪጅኑ የቴክኒሻኖች የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ የማስፋፊያ ሥራዎችን እያከናወነ ነው

ሪጅኑ የቴክኒሻኖች የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ የማስፋፊያ ሥራዎችን እያከናወነ ነው

የሰሜን ምስራቅ 1 ሪጅን በሥሩ ለሚገኙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሠራተኛ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶችን እየገነባ እንደሚገኝ አስታወቀ።

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ በድሩ አህመድ እንደገለፁት የሸዋ ሮቢት እና የኮምቦልቻ 1 ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ያለባቸውን የሠራተኛ መኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ስምንት አዲስ የመኖሪያ ቤቶች በመገንባት ላይ ናቸው።

የቤቶች ግንባታ 70 በመቶ የተከናወነ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ ቤቶቹ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

ለሪጅኑ አገልግሎት እንዲሰጥ የተገነባው 300 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የመጋዘን ግንባታ 90 በመቶ መድረሱንም ነው ያስታወቁት።

ለኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የታወር አካላት እና ለኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የመለዋወጫ ዕቃዎች ማስቀመጫ የሚያገለግሉ ውጫዊ መጋዘኖች (Out door warehouses) በኮምቦልቻ አንድ እና ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በዓለም ከተማ ማከፋፈያ ጣቢያ የነባር መኖሪያ ቤቶች ዕድሳት መከናወኑን ገልፀው፣ በከሚሴ፣ በሸዋ ሮቢት በኮምቦልቻ አንድ እና ሁለት ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች አዲስ የጥበቃ ማማዎች እየተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ አቶ በድሩ ገለፃ በሸዋሮቢት እና በኮምቦልቻ አንድ ማከፋፈያ ጣቢያዎች  የኮንክሪት አስፓልት የውስጥ ለውስጥ መንገድ ተገንብቷል።

በሸዋ ሮቢት፣ በከሚሴ፣ በኮምቦልቻ አንድ እና ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ደግሞ የትራንስፎርመሮችንና ሌሎች መሳሪያዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያግዙ የጠጠር ማንጠፍ ሥራ መከናወኑንም ነው የገለፁት።

Scroll to Top