በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ለተውጣጡ የኦፕሬሽን ባለሙያዎች የዲጂታል መሣሪያዎችን የመጠቀም ልምምድንና እውቀትን (Digital Mindset and Literacy) ለማሳደግ ለአስር ቀናት ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል፡፡
በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጽዮን በቀለ እንደገለጹት በተቋሙ ከተለዩ የለውጥ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በመሆኑ በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ሠራተኞች በዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ላይ ያላቸው አስተሳሰብና እውቀት አነስተኛ መሆን ተቋሙ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶች በአግባቡ በመተግበር ውጤት ለማስመዝገብ አዳጋች እንዳደረገበት በጥናት መለየቱን ተናግረዋል፡፡
ይህን ክፍተት በዘላቂነት በመቅረፍ ሠራተኞች በቀጣይ ከሚመጡ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲላመዱ እንዲሁም በተቋሙ ወደ ሥራ የገቡ ሲስተሞችን ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበሩ ለማስቻል ሠልጠኞችንና የሥልጠና ርዕሰ ጉዳዮችን በመለየት ሥልጠናዎች በዙር እየተሰጡ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ሥልጠናው በተለይም በተቋሙ የኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ክህሎታቸውን በማዳበር የአሰራር ሥርዓቶች ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚረዳ መሆኑንም አንስተዋል፡፡


አሁን ላይ የደረጃ እድገትና የቅጥር ፈተናዎችን ጨምሮ የተቋሙ ሥራዎች ወደ ዲጅታል እየተለወጡ መሆኑን ያስታወሱት ወ/ሮ ጺዮን ወደ ዲጅታል ትራንስፎርሜሽን የሚደረግ ጉዞ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ በመሆኑ ሠራተኞች የዲጅታል መሣሪያዎችን መጠቀም የሚያስችል ዕውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በሦስተኛው ዙር ሥልጠናውን ወስደው ያጠናቀቁ ባለሙያዎች ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ውጤት ለማስመዝገብ መትጋት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ሥልጠናውን ላጠናቀቁ ባለሙያዎች ሰርትፊኬት የተሰጠ ሲሆን በቀጣይ ዙርም ሥልጠናው ለሌሎች ሠራተኞች የሚሰጥ ይሆናል፡፡


