‎ማከፋፈያ ጣቢያው ለደቡባዊ ግሪድ ዋነኛ የኃይል ማዕከል በመሆን እያገለገለ ነው፤

‎ማከፋፈያ ጣቢያው ለደቡባዊ ግሪድ ዋነኛ የኃይል ማዕከል በመሆን እያገለገለ ነው፤

‎በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የወላይታ ሶዶ ሁለት ባለ 400 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ለአካባቢውና ለደቡባዊ ግሪድ ዋነኛ የኃይል ማዕከል በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝ የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።
‎
‎ሥራ አስኪያጁ አቶ በላይነህ ህንዳሞ እንደገለጹት ጣቢያው ከጊቤ ሦስት የሚመነጨውን 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት ኃይል የሚቀበል ሲሆን ከግልገል ጊቤ ሁለት እንዲሁም በይርጋለም ቁጥር ሁለት በኩል ደግሞ ከገናሌ ዳዋ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው።
‎
‎ከኃይል ማመንጫዎች ከሚቀበለው ኃይል ውስጥ 60 ከመቶ የሚሆነውን በቀጥታ ለገላን ማከፋፈያ ጣቢያ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
‎
‎በባለ 132 ኪሎ ቮልት ለሀላባ እና ለወላይታ ቁጥር አንድ፣ በባለ 230 ኪሎ ቮልት ለአዲሱ የአርባ ምንጭ ቁጥር ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያዎች እንዲሁም በ33/15 ኪሎ ቮልቶች ለዳታ ማይኒንግ ድርጅቶችና ለኢትዮጵያ ኤእሌክትሪክ አገልግሎት የአካባቢው ዲስትሪክት እንደሚያቀርብም ጠቁመዋል።


‎
‎አንደ አቶ በላይነህ ገለጻ በተጨማሪም ጣቢያው በአራት ባለ 400 ኪሎ ቮልት መስመር ለኢትዮ-ኬንያ ኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ይሰጣል።
‎
‎የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለማረጋገጥ የቅድመ ፍተሻ፣ የድንገተኛና በዕቅድ ላይ የተመሰረቱ የክትትልና የጥገና ሥራዎች ከሪጅኑ ጋር በመተባበር እየተከናወኑ በመሆኑ በአቅርቦት በኩል ምንም ዓይነት ስጋት እንደሌለ አብራርተዋል።
‎
‎የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የወላይታ ሶዶ ሁለተኛ ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ሥራ ተጠናቆ ወደ ኦፕሬሽን መግባቱንም ገልጸዋል።
‎
በአሁኑ ወቅት ጣቢያው እያንዳንዳቸው 250 ሜጋ ቮልት አምፒዬር አቅም ያላቸው ሦስት አውቶ ትራንስፎርመሮች ያሉት ሲሆን አጠቃላይ አቅሙም 750 ሜጋ ቮልት አምፒዬር መድረሱ ተናግረዋል።


‎
‎ከእነዚህ ትራንስፎርመሮች መካከል ሁለቱ የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ አካል ለሆኑት ለአርባምንጭ ቁጥር ሁለት እና ለሽግዳን ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተብለው በቅርቡ የተገጠሙ መሆናቸውን አንስተዋል።

‎ጣቢያ አሁን ላይ ተጨማሪ የኃይል ጥያቄዎችን በብቃት ማስተናገድ የሚችል አቅም ያለው ቢሆንም በቀጣይ ሊኖሩ የሚችሉ የኃይል ፍላጎቶችን ታሳቢ በማድረግ አቅሙን ይበልጥ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
‎
‎በዚህም መሠረት በ2019 በጀት ዓመት ተጨማሪ ባለ 250 ሜጋ ቮልት አምፒዬር አውቶ ትራንስፎርመር ለመትከል የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።
‎
‎የወላይታ ሶዶ ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያ ለደቡባዊ ግሪድና ለኢትዮ ኬኒያ ኮንቨርተር ዋነኛ የኃይል ማዕከል በመሆኑ ከመለዋወጫ እቃ እጥረት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ በላይነህ አሳስበዋል።

Scroll to Top