የዓለም አቀፍ የሥራ ላይ ደህንነትና ጤና ቀን “ጤናማ የሥነ-ልቦናና ማህበራዊ የሥራ አካባቢን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃል በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ትናንት በውይይት ተከብሯል።
በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ተወካይ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያለውአይቀር ማንደፍሮ በውይይቱ መድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለፁት ሠራተኞች የደህንነትና የጤና ጥበቃ መመሪያዎችን ባለመከተላቸው ለተለያዩ የአካል ጉዳቶችና ለሕይወት ማጣት ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡

በመሆኑም ሁሉም ሠራተኞች ለራሳቸውና ለሥራ ባልደረቦቻቸው ደህንነት ትኩረት በመስጠት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በኮርፖሬት ፕላኒንግ የሥራ ላይ ደህንነትና ጤና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኮርሳ ታሬሳ በበኩላቸው በሥራ ቦታ ከሥራ ይዘት ሁኔታና አደረጃጀት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ከፍተኛ የሥራ ጫና፣ የሥራ መብዛት፣ ፍጥነትና ድግግሞሽ ያለባቸው ተግባራት እንዲሁም የሥነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ችግሮችለሥራ ላይ አደጋዎች አጋላጭ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ የሥራ አካባቢ መፍጠር ለምርታማነት መጨመርና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና ስላለው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ሲሉ ሥራ አስኪያጁ አሳስበዋል።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ቦታዎች ቁጥጥርና የሙያ ደህንነትና ጤንነት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ ጥሩዓለም በለጠ በንግግራቸው ጤናማ የሥራ አካባቢ መፍጠር የሰብዓዊ መብት ጥያቄ መሆኑን በመጥቀስ ተቋማት ለሥነ-ልቦናዊ ደህንነት ትኩረት በመስጠት ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን አዳዲስ የሥራ ላይ ጤና ስጋቶች ለመከላከል አሠሪዎችና ሠራተኞች በቅንጅት የመከላከያ ስልቶችን መተግበር እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ውይይቱን የመሩት የተቋሙ የሰው ሀብት ሥራ አስፈፃሚ አቶ አታላይ አበበ እንደተናገሩት ተቋሙ ለሠራተኞች ደህንነትና ጤና ጥበቃ የሚመደበውን በጀት ለታለመለት ዓላማ ብቻ በማዋል የቅድመ መከላከል ሥራዎችን እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።

አደጋ ከተከሰተ በኋላ ከሚወጣው ከፍተኛ የሕክምናና የካሳ ወጪ ይልቅ፣ ጥራት ያላቸው የመከላከያ ቁሳቁሶችን በማቅረብና ቀጣይነት ያለው የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት አደጋን አስቀድሞ መከላከል ለተቋሙም ሆነ ለሠራተኛው ዋስትና መሆኑን አቶ አታላይ ተናግረዋል።
የጤናና ደህንነት ባለሙያዎችም ኃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡና በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎችም ለደህንነት መመሪያዎች ተገዥ በመሆን እንዲሁም ጥብቅ ክትትል በማድረግ በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋን ለመቀነስ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።


