
ከኮምቦልቻ 2 ወደ ኮምቦልቻ 1 ማከፋፈያ ጣቢያ በተዘረጋው ባለ 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ በተፈፀመ ዝርፊያ ዛሬ ከረፋዱ 5:30 ሰዓት አካባቢ በአንዳንድ አካባቢዎች ኃይል ተቋርጧል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምስራቅ አንድ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ በድሩ አህመድ እንደገለፁት በኮምቦልቻ ከተማ አቅራቢያ በተፈፀመው ዝርፊያ አንድ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ሲወድቅ ሌላኛው ተፈታቶ ከመውደቁ በፊት ተደርሶበታል።
በዚህ የተነሳ በኮምቦልቻ ከተማና አካባቢው፣
በደሴ ከተማና አካባቢው፣ በአቀስታ ከተማና አካባቢው እንዲሁም በዓለም ከተማና አካባቢው ኃይል መቋረጡን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
የኮምቦልቻ ቁጥር አንድ ማከፋፈያ ጣቢያ ወደ ደሴ በ66 ኪሎ ቮልት፣ ወደ አቀስታ እና ዓለም ከተማ ማከፋፈያ ጣቢያዎች በ132 ኪሎ ቮልት እንዲሁም ለኮምቦልቻ ከተማ በ15 ኪሎ ቮልት ኃይል ሲሰጥ ነበር።
የወደቀውን የብረት ምሰሶ መልሶ ለማቆምና የመውደቅ ስጋት ያጠላበት ሁለተኛውን ምሰሶ በሌሎች ድጋፎች መልሶ ለማቆም ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ ህብረተሰቡ ችግሩን ተገንዝቦ በትዕግስት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”