👉 በዛሬው ዕለት በሀገር አቀፍ ደረጃ “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ታሪካዊ ዘመቻ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሠራተኞች፣ የአሉቶ ጂኦተርማል ቁፋሮ ፕሮጀክት ሰራተኞችና የፀጥታ አካላት እንዲሁም የሰሜን ምሰራቅ -2 ሪጅን ሰራተኞች ባሉበት አካባቢ የችግኝ ተከላ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሠራተኞች በፕሮጀክቱ መገኛ ስፍራ ከአይሻ ወረዳ አመራሮች ጋር ችግኝ ሲተክሉ የአሉቶ ጂኦተርማል ቁፋሮ ፕሮጀክት ሠራተኞች ደግሞ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ችግኝ ተክለዋል፡፡
በተመሳሳይ የሰሜን ምሰራቅ 2 ሪጅን ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ አይሮልአፍ ቀበሌ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈዋል፡፡
የችግኝ ተከላው ተቋሙ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
የታዳሽ ኃይል ልማትና የሥነ-ምህዳር መልሶ ማገገም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ተመጋጋቢ መሠረቶች መሆናቸውን ያምናል።
ኢትዮጵያ እ.ኤአ. በ2027 ዓ.ም. የCOP32 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤን ለማስተናገድ በምትዘጋጅበት ወቅት የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብሩ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጥበቃ እርምጃ ውስጥ የመሪነት ሚናዋን ለማሳየት ዕድሉን ይፈጥራል፡፡
ዛሬ የምንተክለው እያንዳንዱ ችግኝ የነገዋን ለም፣ አረንጓዴና ብሩህ ኢትዮጵያን የመገንባት ተስፋችን በማደስ ለንጹህ ኃይል ልማት፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለካርቦን ገበያ እድሎች እና ለበለፀገች ኢትዮጵያ መጪ ትውልድ የምናደርገው ውድ ኢንቨስትመንት ነው።








