ማመንጫ ጣቢያው በበጀት ዓመቱ ከ940 ጌጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል አመንጭቷል

ማመንጫ ጣቢያው በበጀት ዓመቱ ከ940 ጌጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል አመንጭቷል


ሥራ አስኪያጁ አቶ ደሳለኝ ንጉሳ እንደተናገሩት ጣቢያው በ2018 በጀት ዓመት ለማመንጨት ካቀደው 986 ጌጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 943 ጌጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማመንጨት የዕቅዱን 95 ነጥብ 63 በመቶ አሳክቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ከዕቅዱ የ43 ጌጋ ዋት ሰዓት ወይም የ4 ነጥብ 37 በመቶ እንዲሁም ከባለፈው የ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ34 ጌጋ ዋት ሰዓት ወይም የ3 ነጥብ 6 በመቶ ቅናሽ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጣቢያው ሶስቱም ተርባይኖች አስፈላጊው ዓመታዊ ጥገና ተከናውኖላቸው ኃይል ለማመንጨት ዝግጁ ቢሆኑም የዘንድሮው ክረምት ዘግይቶ መግባቱን ተከትሎ ለቀጣዩ የ2019 በጀት ዓመት በግድቡ የተሻለ ውሃ ለመያዝ ሲባል በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ወር ላይ ኃይል ማመንጨት በመቀነሱ አፈፃፀሙ የተወሰነ ዝቅ ማለቱን አቶ ደሳለኝ ጠቅሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ኃይል ከማመንጨት ሥራዎች በተጨማሪ በተርባይን፣ በጀነሬተር፣ በተርባይኑ የማቀዝቀዣ ሥርዓት፣ በፓወር ትራንስፎርመር እና በሌሎች የተለያዩ አካላት ላይ በራስ አቅም የጥገና ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

የጥገና ሥራው ተርባይኖቹ በሙሉ አቅማችው እንዲሰሩ፣ የዕቃዎች ብልሽት እና የተለያዩ ፍሳሾች እንዲቀንሱ በማድረግ በኦፕሬሽን ሥራው ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

በ1996 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጊቤ አንድ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 184 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አለው፡፡

Scroll to Top