ተቋሙ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን ለማረጋገጥ የግሪድ ማጠናከሪያ ጥናት አከናውኗል

ተቋሙ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን ለማረጋገጥ የግሪድ ማጠናከሪያ ጥናት አከናውኗል


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ከኮፕ-32 ጋር ተያይዞ ለአዲስ አበባና አካባቢዋ ተጨማሪ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል የግሪድ ማጠናከሪያ ጥናት ማከናወኑን አስታወቀ፡፡

በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ ተወካይ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ያለውአይቀር ማንደፍሮ እንደገለፁት‎ በበጀት ዓመቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን የሚጨምሩ እንዲሁም የግሪድ ሲስተም አስተማማኝነትን የሚያሻሽሉ ሦስት ፕሮጀክቶችን የቴክኒካዊ የአዋጭነት ጥናቶች ተከናውነዋል፡፡

የአራት አነስተኛ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የቅድመ አዋጭነት ጥናት 50 በመቶ ለማከናወን ታቅዶ የዕቅዱን 90 በመቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከአምስት ዓመት በፊት ተዘጋጅቶ የነበረውን የቴክኖሎጂ ካታሎግ የመከለስ ሥራ ከዴንማርክ እና ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ጋር በጥምረት መከናወኑን የጠቆሙት ሥራ አስፈጻሚው ረቂቅ ሰነዱ የመጨረሻ ግብዓት ለመሰብሰብ በሚያመች መልኩ ለውይይት እና ለሕትመት ዝግጁ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ አካባቢ ለሚገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማሟላት እንዲሁም የቂሊንጦ እና የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የረጅም ጊዜ የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ስለመዘጋጀቱም አብራርተዋል።

በተመሳሳይ ለኢትዮጵያ-ጅቡቲ የባቡር ኔትዎርክ አስተማማኝ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል የሲስተም ማሻሻያ ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ተወካይ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ በበጀት ዓመቱ በተቋሙ ከተለዩ 48 ስጋቶች ውስጥ 34 ስጋቶች ላይ የተለያዩ የስጋት ማቅለያ ሥራዎች መከናወናቸውም ነው የተናገሩት።

ከከፍተኛ አመራሩ ተገቢ ድጋፍ መኖሩ፤ የሀገር ውስጥ ኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት መጨመሩ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ፍላጎቶች መኖር፤ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋሮች እና አማካሪ ድርጅቶች ጋር በትብብር መስራት በበጀት ዓመቱ የታዩ መልካም አጋጣሚዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

Scroll to Top