የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተለያዩ የኃይል አማራጮችን በማስፋት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢነርጂ አቅም መገንባት እንዳለበት የመከላከያ ሚኒስትርና የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ አባል ኢንጂነር አይሻ መሐመድ አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ አመራር ቦርድ የተቋሙን የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ሲገመግም ኢንጂነር አይሻ እንደገለጹት ተቋሙ በጀት ዓመቱ በቁጥር ደረጃ መልካም ውጤት ያሳየ ቢሆንም በሂደቱ የታዩ ጉድለቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በዝርዝር መተንተን አስፈላጊ ነው፡፡
በቀጣይ ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የውሃ እና የኃይል አቅርቦት እጥረቶችን እንዲሁም እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የኃይል አቅርቦት ፍላጎቶችን በብቃት ለማስተዳደር የሚያስችሉ ስልቶችን በመተግበር እንደ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያሉ ሥነምህዳር ላይ ያተኮሩ መፍትሔዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ፈቃዱ ደግፌ እንደተናገሩት የፕሮጀክቶች አፈጻጸምና የፋይናንስ ዕቅድ ተቋሙ ባስቀመጠው አቅጣጫ መመራት አለበት፡፡

የሀገር ውስጥና የውጭ ብድሮችን ለመክፈል የሚያስፈልገውን ከፍተኛ የምንዛሪ ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የፋይናንስ ስትራቴጂ በጥንቃቄ ሊቀረጽ እንደሚገባም ገልፀዋል።
የተቋሙ የሠራተኛ ማህበር የኦዲት ፀሐፊና የሥራ አመራር ቦርድ አባል ወ/ሮ ማህሌት ንጉሥ በበኩላቸው የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም የተሻለ ቢሆንም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን ለማሳካት አዳዲስና የተለዩ ስትራቴጂዎችን መከተል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ጫና ለመቋቋም ከተለመደው አሰራር በመውጣት አማራጭ የኃይል ምንጮችን ለመጠቀም ማቀድ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
የተቋሙ የሠራተኛ ማህበር የኦዲት ሰብሳቢና የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ተሾመ በላይ እንደገለፁት ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ለመጀመሪያ ጊዜ ላስመዘገበው ትርፍ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ሊመሰገኑ ይገባል።

የተቋሙ ዋና ዓላማ ኃይል ማመንጨት፣ ማስተላለፍ እና መሸጥ ቢሆንም ከዚህ ጎን ለጎን የሠራተኛውን የሥራ አካባቢ ማሻሻል ሠራተኛውን ማብቃትና ማበረታታት ለተቋሙ ስኬት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።



