ከኃይል ማመንጫዎች ግድቦች የሚመነጨውን አንድም ኪሎ ዋት ኃይል ያላግባብ እንዳይባክን ጥብቅ የውሃ አስተዳደር ሥርዓት እንደሚዘረጋ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጹ፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ባቀረቡት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዋና ዋና ዕቅዶች ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት ባለፈው በጀት ዓመት ተቋሙ የጀመረው የማንሰራራት ጉዞ ወደ ኋላ እንዳይመለስ አመራሩና ሠራተኛው በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል።

የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳይቀንስ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በስፋት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የተቋሙ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መዘገየት ከተቋም ስኬት አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ተግዳሮት እንደሚሆን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሁሉም ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜና የጥራት ደረጃ መጠናቀቅ እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ በተለይ በራስ አቅም እና በሥራ ተቋራጮች በተያዙ ፕሮጀክቶች ላይ የሚታዩ የአፈጻጸም ጉድለቶችን ማረም ይገባል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን፣ የሥነ-ምግባር ግድፈቶችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቀጥታ ለዋና ሥራ አስፈጻሚው ማሳወቅ የሚያስችል ዲጂታል የቁጥጥር ሥርዓት እንደሚዘረጋ ጠቁመዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በፕሮጀክት አፈጻጸምና በኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ ካጋጠሙ ችግሮች ትምህርት በመውሰድ እና ወጪ ቆጣቢ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የተጀመረውን የስኬት ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል።

ተቋሙ በቀጣይ የሚያመርተው ኢነርጂ ሳይባክን ወደ ሀብት እንዲቀየር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ጨምሮ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ለመሥራት እና የተቀናጀ ቁጥጥር ለማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን አብራርተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለተመዘገበው ስኬት ለአመራሩና ለሠራተኛው ምስጋናቸውን ያቀረቡት ኢንጂነር አሸብር በቀጣይ በጀት ዓመትም ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀምና ሥጋቶችን ወደ ዕድል በመቀየር የተቋሙን ግብ ለማሳካት በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

