ግድቡ “የሚሊየኖችን ቤት ወደ ብርሃን ቀይሯል” – ሲኤንኤን

ግድቡ “የሚሊየኖችን ቤት ወደ ብርሃን ቀይሯል” – ሲኤንኤን

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ “የሚሊየኖችን ቤት ወደ ብርሃን የቀየረ ግድብ ነው” ሲል ዓለም አቀፉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲ ኤን ኤን ዘገበ፡፡

በሲኤንኤን የኬንያ ዘጋቢ ቪክቶሪያ ሩባደሪ ወደ ህዳሴ በመጓዝ ባሰናዳችው ዘገባ ግድቡን ኢትዮጵያውያን ያለማንም ድጋፍ በራሳቸው አቅም ገንብተው ለውጤት ማብቃታቸውን ገልፃለች፡፡

በአፍሪካ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው የኃይል አቅርቦት ትስስር ሚናው ከፍተኛ መሆኑን በፕሮግራምዋ አንስታለች፡፡

ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ኃይል ከማቅረብ ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ በመሆን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በመደገፍ ረገድ ትልስ ተስፋ ይዞ እንደመጣ አብራርታለች፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በዘገባው ላይ ግድቡ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤት ሀገራትን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይ ደግሞ ለሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ኃይል ለመሸጥ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 145 ሜትር ከፍታ እና 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው በዓመት በአማካይ 15 ሺህ 670 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ያመነጫል፡፡

Scroll to Top