ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከ305 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል

ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከ305 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ከ305 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባራትን ማከናወኑን በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት ተቋሙ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ጎን ለጎን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የፋይናንስ ወጪ በማድረግ ለመቄዶኒያ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ማዕድ ማጋራቱን ተናግረዋል፡፡

በኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ ዙሪያ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ለተጀመሩት ሥራዎች 123 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ሞገስ ገለፃ ተቋሙ በደሴ ከተማ ከ29 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለ6 አቅመ ደካማ አባውራዎችና እማውራዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተቋሙ በአጠቃላይ 305 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የፋይናንስ ወጪ በማድረግ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን ማከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ በሰጠዉ አቅጣጫ መሰረት የኮርፖሬት ማህበራዊ ኃላፊነት የአፈጻጻም መመሪያ ጸድቆ  ወደ ሥራ መግባቱን የገለፁት አቶ ሞገስ  ተቋሙን ከሕብረተሰቡ ጋር ይበልጥ የሚያስተሳስሩ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

Scroll to Top