በጋሞ ዞን ቁጫ ወረዳ በሚገኝ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ከባድ የስርቆት ወንጀል የፈጸመውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የወረዳው ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አዳነ ቡርጄ እንደገለጹት ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 አካባቢ ከወላይታ ሶዶ-ሳውላ በተዘረጋው ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ የስርቆት ወንጀል የፈጸመውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል ሲደረግ ቆይቷል፡፡


ተጠርጣሪው ከ7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት በተለያዩ ጊዜያት በባለ ሦስት እግር ባጃጅ በማጓጓዝ በቁጫ ወረዳ ጋሌ 2 ቀበሌ ልዩ ሥፍራ ሞጎላ ማዞሪያ ከሚባል አካባቢ ከደበቀበት ቦታ በሕብረተሰቡ ጥቆማ ፖሊስ ንብረቱን በቁጥጥር ሥር መዋሉን ጠቁመዋል።
ተጠርጣሪው አቶ ተሾመ ቆልቻ በቅጽል ስሙ ክርክያዉ ለጊዜው ከአካባቢው ቢሰውርም ፖሊስና የሚሊሻ አባላት ባደረጉት ከፍተኛ ክትትል በቁጥጥር ሥር ውሉ በከባድ የኃይል መሰረተ ልማት ስርቆት ወንጀል ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በወጣባቸው የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ከማስከተላቸውም ባሻገር የኃይል መቋረጥን በማስከተል በህብረተሰቡ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያደርሱ አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም ሕብረተሰቡ በኃይል መሠረተ ልማት ላይ ስርቆት የሚፈጽሙ አካላትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ኢንስፔክተር አዳነ አሳስበዋል፡፡
በተመሳሳይ የተሰረቁ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ገመዶች በጠገዴ ወረዳ ሶሮቃ ኬላ በተደረገ ፍተሻ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አስታውቋል።
ጽ/ቤቱ እንዳስታወቀው መነሻውን ዳንሻ ከተማ በማድረግ ወደ ጎንደር ሲጓዝ በነበረና የሰሌዳ ቁጥሩ A28673 በሆነ አስር ጎማ ተሽከርካሪ ላይ የተጫነ 50 ኩንታል ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ የአልሙኒየም ኬብል በሶሮቃ ኬላ በተደረገ ፍተሻ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ኬብሉን በመቆራረጥ እና በማዳበሪያ ከረጢቶች ውስጥ በማሸግ፣ በሩዝ በመሸፈን ወደ ጎንደር ለማጓጓዝ ሲሞክሩ በኬላው በተካሄደ ጥንቃቄ የተሞላ ፍተሻ ሙከራቸው መክሸፉንና በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑም ተመላክቷል።
የሕዝብና መንግሰት መሰረተ ልማቶችን ለመጠበቅ የሚያደርገውን የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል የገለጸው የፖሊስ መምሪያ ሕብረተሰቡም እንዲህ ያሉ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት መረጃ በወቅቱ ለፀጥታ ኃይሎች በመስጠት ከፖሊስ ጋር ያለውን ትብብር እንዲያጠናክር ጥሪውን አቅርቧል።
የኢነርጂ አዋጅ 810/2006 አንቀጽ 26 በኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ ወይም ማከፋፈያ ተቋማት ላይ ጉዳት ያደረሰ ማንኛውም ሰው ከ5 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡


