ጥራት ያለው ሪፖርት የተቋሙን ገጽታ ከመገንባት ባሻገር የሀብት አጠቃቀምን ለማሻሻል እንደሚረዳ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ተናገሩ

ጥራት ያለው ሪፖርት የተቋሙን ገጽታ ከመገንባት ባሻገር የሀብት አጠቃቀምን ለማሻሻል እንደሚረዳ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ተናገሩ

ጥራት ያለው ሪፖርት የተቋሙን ገጽታ ከመገንባቱ ባሻገር የሀብት አጠቃቀምን ለማሻሻል እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ የሥራ አመራር ቡድን እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በጋራ በመሆን በሪፖርት ዝግጅትና አቀራረብ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አካሂደዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የኢነርጂ እና ኮኔክቲቪቲ ፖርትፎሊዮ ዳይሬክተር ዶክተር ጌትነት መላክ በሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ላይ ያተኮረ የንድፈ-ሐሳብ እና ገቢራዊ ተሞክሮዎችን ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡

የምክክር መድረኩ የተቋሙን አጠቃላይ የሪፖርት አቀራረብ ለማሻሻልና ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ጌትነት ምክክሩ በተቋሙ የተከናወኑ ተግባራትን፣ የተገኙ ውጤቶችን እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በግልጽ ለማሳየት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ሪፖርት ማቅረብ በቀላሉ መረጃ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ የተቋሙን ትክክለኛ ነባራዊ ሁኔታ እና የዕድገት ደረጃ ለባለድርሻ አካላት የሚያሳይ ዐቢይ መሳሪያ መሆኑንም ነው የገለፁት።

የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችም ተቋሙ በኃይል ማመንጨት፣ በማስተላለፍ፣ በኃይል ሽያጭ እና በፕሮጀክት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በተደራጀ እና ግልፅ በሆነ መንገድ በማቅረብ የመሪነት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

ዶክተር ጌትነት እንደተናገሩት ሁሉም የተቋሙ የሥራ ክፍሎች ወቅታዊ እና ጥራት ያለው ሪፖርት ማቅረብ ካልቻሉ ተቋሙ ሊያሳካ ያቀደውን ራዕይ እና ተልዕኮ ከግብ ማድረስ አይችልም፡፡

የኮርፖሬት ፋይናንስ፣ የኦፕሬሽን እና የስትራቴጂክ ዕቅዶችን ከማዘጋጀት በተጨማሪ የሩብ ዓመት እና ዓመታዊ የአፈፃፀም ሪፖርቶችን ለሚመለከታቸው አካላት በወቅቱ ማድረስ እንደሚገባ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው የየዕቅድ እና የክዋኔ ሪፖርቶች ጥራት ባለው መልኩ በተያዘላቸው ጊዜ ሊዘጋጁ ይገባል ብለዋል፡፡

ጥራት ያለው ሪፖርት የተቋሙን ገጽታ ከመገንባቱ ባሻገር የሀብት አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እና ወደፊት የሚወሰዱ የፖሊሲ እና የስራ መመሪያዎችን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ትክክለኛ እና ወቅታዊ ሪፖርት ለሀገራዊ ውሳኔዎች፣ ለፋይናንስ እና ለደንብ ማዕቀፎች ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ያስረዱት ዋና ስራ አስፈጻሚዉ ሁሉም የሥራ መሪ ጥራት ያለው የሥራ ዕቅድ እና የአፈጻጸም ሪፖርት በወቅቱ ማቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል።

Scroll to Top