ተቋሙ ከዋና ተልዕኮው ጎን ለጎን የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል

ተቋሙ ከዋና ተልዕኮው ጎን ለጎን የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከተሰጠው የኃይል ማመንጨትና ማስተላለፍ ሀገራዊ ተልዕኮ ባሻገር የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የማህበራዊ ኃላፊነት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንደገለፁት ኃይል ማመንጫት አስከ ማከፋፈያ ጣቢያ ማድረስ፣ ኃይል ማመንጫዎችን፣ ከ132 ኪሎ ቮልት በላይ የሆኑ ማከፋፈያ ጣቢያዎችና ማስተላለፊያ መስመሮችን መገንባት እንዲሁም ኃይልን በጅምላ ለደንበኞች ማቅረብ በአዋጅ የተሰጡት ዋና ዋና ተግባራት ናቸው። ተቋሙ እነዚህን አገራዊ ኃላፊነቶች በብቃት ከመወጣት ጎን ለጎንም የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚያስችሉ ተጨባጭ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የማህበረሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በ40/60 የመጋራት ፖሊሲ መሰረት ባለፉት በጀት ዓመታት ተቋሙ ከ535 ሚሊየን 354 ሺህ ብር በላይ በመመደብ የመልካ ዋከና ኃይል ማመንጫ ጣቢያ አዋሳኝ መንደሮች፣ የአዳማ ከተማ የዳካ አዲ፤ የኮሌ አቦ ቱሉ ሙጢና የቦሌ ለሚ፣ የደብረ ብርሃን ማከፋፈያ ጣቢያዎች አካባቢ ለሚገኙ ነዋሪች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ኃላፊው አብራርተዋል።

በተመሳሳይ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመትም ከ396 ሚሊዮን 528 ሺህ ብር በላይ በጀት በመመደብ በጊቤ 3 አካባቢ ለሚገኙ 24 ቀበሌዎች እና በበለስ አካባቢ ለሚገኙ ነዋሪዎች የኃይል አቅርቦት ለማድረስ የግንባታ ስራ ጀምሯል። በተጨማሪም ህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ባለቤት ለማድረግ በተከዜ ኃይል ማመንጫ አካባቢ ለሚገኙ 10 መንደሮች የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልፀዋል።

እንደ አቶ ሙላት ገለፃ በሁሉም ሪጂኖችና ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ችግኝ ከመትከል በተጨማሪ ባለፈው በጀት ዓመት በኦሮሚያ ክልል አዳሚ ቱሉ ጂዶ፤ በአማራ ክልል ደሴ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የም ዞን ፎፋ ከተማ ከ39 ሚሊየን ብር በላይ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና የትምህርት ቤት እድሳት ስራ ተከናውኗል፡፡ እንዲሁም በደሴ ከተማ ለሚገኙ 6 አቅመ ደካሞች ባለ አንድ ወለል ዘመናዊ የመኖሪያ ህንፃ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ግንባታው ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዘንድሮው በጀት ዓመትም በአሪ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ችግኝ የመትከል፣ ሰባት ትምህርት ቤቶችና ሰባት የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የማደረግ እንዲሁም በሶማሌ ክልል በአይሻ ወረዳ የሚገኝ ትምህርት ቤት እድሳት ስራ ለማከናወን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ሙላት ጠቅሰዋል።

ከስራ ዕድል ፈጠራ እና የህብረተሰብ ማቋቋም አኳያ ለዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ተቋሙ የጎላ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል ያሉት ኃላፊው በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ወቅት የሚወጡ ተረፈ ምርቶችና ቁርጭራጭ ብረቶች ለህብረተሰቡ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ አስችሏል።

እንደ አቶ ሙላት ገለፃ ተቋሙ የካሳ ክፍያን የስራዎች መነሻ እንጂ መድረሻ አድርጎ አይወስደውም። በመሆኑም ከልማት ቦታዎች የሚነሱ ወገኖች ተደራጅተው እሴት በሚጨምሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሰማሩ በተደራጀው የስራ ክፍል በኩል ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ለአቅመ ደካሞች፣ ለሴቶችና ለወጣቶች ወደ ተቋሙ በቅጥር የሚቀላቀሉበትን አሰራር ለማመቻቸት ልዩ የድጋፍ ስርዓት የተዘረጋ ሲሆን ከአካባቢ መስተዳደር አካላት ጋር በመቀናጀትም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የስራ እድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ ተመቻችቷል።

ተቋሙ በተለያዩ አደጋዎችና ማህበራዊ ፍላጎቶች ወቅት በላይ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ያወሱት አቶ ሙላት ከስምንት ሚሊየን ብር በላይ ወጭ በማድረግ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተከስቶ በነበረው የመሬት መንሸራተት አደጋ፣ በአፋር ክልል ለታካሚዎች የሚውል የአምቡላንስ ተሸከርካሪ ድጋፍ፣ ለመቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ ማዕከልና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደርጓል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገትና ለማህበራዊ እንቅስቃሴዎች የማይተካ ወሳኝ ግብአት በመሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተጣለበትን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንዲችል ህብረተሰቡ የባለቤትነትና የኔነት ስሜት በማሳደር ለኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግ የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

Scroll to Top