🌉 ወደ ተጨባጭ ልማት – የኮይሻ ፕሮጀክት ከኃይል ማመንጨት ባሻገር ያለው ፋይዳ 🇪🇹

🌉 ወደ ተጨባጭ ልማት – የኮይሻ ፕሮጀክት ከኃይል ማመንጨት ባሻገር ያለው ፋይዳ 🇪🇹

 የኦሞ ወንዝን ለመሻገር ስጋትና ፍርሃት ይጋረጣቸው የነበሩ ማኅበረሰቦች፤ ዛሬ በድልድይና በአዳዲስ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ተገናኝተዋል።
የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ባሻገር በአካባቢው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ በገበያ፣ በቱሪዝምና በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድ ምን ለውጦችን አስገኝቷል?
📌 በዚህ የጽሑፋችን ሁለተኛ ክፍል ፕሮጀክቱ በአካባቢው ማኅበረሰብ ሕይወትና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ስላለው ፋይዳ እንቃኛለን።
 
👇 የኮይሻን የልማት ታሪክ አብረን እንመልከት!
 
ፕሮጀክቱ በአካባቢው ከመገንባቱ በፊት ለዘመናት በኦሞ ወንዝ ማዶና ማዶ ሆነው ይኖሩ የነበሩት የዳውሮ፣ የኮንታ እና የጎፋ ህዝቦች ወንዙን ለመሻገር ይከፍሉ የነበረው መስዋዕትነት እጅግ መራራ ነበር።
 
ዓመቱን ሙሉ ከፍተኛ የውሃ መጠን ይዞ የሚጓዘው የኦሞ ወንዝ ቁጣውን በሚያሳይበት ወቅት ለአካባቢው ማህበረሰብ ከወንዙ ማዶ ያለውን ወገንና ዘመድ ለመጠየቅ በዋና መሻገር ግድ ይላቸው ነበር። በዋና የሚሻገሩት ሰዎችም በሰላም መሻገራቸውን በስጋት ለሚጠባበቁት ወገኖቻቸው ለማሳወቅ በወንዙ ማዶ እንጨት ሰብስበው ጭስ ያጨሱ ነበር። ሆኖም ግን ያ ጭስ ካልታየ… ወይ በአዞ የመበላት ወይም በጎርፍ የመወሰድ አደጋ ደርሷል ተብሎ ስለሚታሰብ ለቅሶና ሰቆቃ ይከተል ነበር።


 
ዛሬ ግን ያ የሰቆቃና የፍርሃት ዘመን ታሪክ ሆኗል!
በፕሮጀክቱ አካልነት በኦሞ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይና አዳዲስ የመንገድ መሠረተ ልማቶች በኦሞ ወንዝ የተካለሉትን የኮንታና የጎፋ ዞኖችን በቀጥታ በማገናኘት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን፣ የገበያ፣ የጤና እና የትምህርት አገልግሎት ተዳራሽነትን አቃንተዋል።
 
ወንዙን ሲሻገሩ ይፈጠር የነበረውን በወንዝ የመወሰድ አደጋ ዛሬ ድልድዩ ታሪክ ቀይሮ በሰላም ለመሻገር በማስቻል የብዙዎችን ህይወት ታድጓል፡፡ ድልድዩ ከባድ የግንባታ ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ ከማገልገሉ ባሻገር የአካባቢው ምርቶች ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚጓጓዙበት ዋና የንግድ ደምስር ሆኗል።
 
የኮይሻ ፕሮጀክት ከኃይል ማመንጨት ባለፈ በ”ገበታ ለሀገር” መርሃ ግብር ትልቅ ትኩረት አግኝቶ የተገነባ በመሆኑ የአካባቢውን ገፅታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል። በግድቡ መገንባት ምክንያት እንደ ሃላላ ኬላ ሎጅ እና ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ነፍስ ዘርተውባቸዋል። ይህም የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን በመሳብ ለአካባቢው ማህበረሰብ አዲስ ገቢና የንግድ እንቅስቃሴ ፈጥሯል።
 
በግንባታው ወቅት ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶችና ነዋሪዎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብአቶች ከአካባቢው በመወሰዳቸው የውስጥ ኢኮኖሚውን አነቃቅቷል። በተጨማሪም በቱሪዝም መዳረሻዎች አካባቢ ሴቶችና ወጣቶች ባህላዊ የእደ-ጥበብ ምርቶችን፣ የአካባቢውን ምግብና አገልግሎት ለጎብኚዎች በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበት የገበያ ዕድል ተፈጥሯል።
 
የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ብርሃን ማመንጫ ብቻ አይደለም። ለዘመናት ተደብቀው የኖሩ ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን ለዓለም ያሳየ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ያጠናከረ፣ የታሪክ ቁስልን በልማት ድልድይ የሻረ ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ነው፡፡
 
ፕሮጀክቱ ተፈጥሮን፣ የምህንድስና ጥበብንና የሰዎችን ትስስር በአንድ ላይ በማጣመር ኢትዮጵያ ባሏት ተፈጥሯዊ ፀጋዎች ተጠቅማ የማህበረሰቧን ብልጽግና ማረጋገጥ የምትችል መሆኗን ያሳየ ህያው አብነት ነው፡፡
 
ውድ አንባቢያን! የዛሬውን ጽሁፋችንን በዚህ አጠናቀቅን። በሚቀጥለው ጽሁፍ በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እስክንገናኝ ድረስ ቸር ሰንብቱ እያልን መልካም ጊዜ እንመኝላችኋለን!

Scroll to Top