የኃይል መሰረተ ልማቶችን ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል የሚያስችሉ ዘመናዊ አሰራሮችን እየተገበረ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዲጂታል ትራስፎርሜሽን ዘርፍ አስታወቀ።
በዘርፉ የሳይበር ሴኪዩሪቲ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጌትነት አድማሱ እንደገለፁት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ጥቅምት የሳይበር ደህንነት ወር ተብሎ ይከበራል፡፡
በዚህ ዓመትም ወሩ ‹‹የሳይበር ጥቃትን በመከላከል የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን እንጠብቅ›› በሚል መሪ ቃል በተቋም ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተቋሙ የሚያጋጥሙ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲሁም ችግሮች ሲያጋጥሙ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ሰዎችን፣ የአሰራር ሥርዓቶችን እና ቴክኖሎጂን በማቀናጀት እየተሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) የኤሌክትሪክ ኃይልን ከሀገሪቱ ወሳኝ የደህንነት መሰረተ ልማቶች አንዱ አድርጎ እንደመደበው የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በመሰረተ ልማቶቹ ላይ የሚቃጣ የሳይበር ጥቃት የሀገራዊ ደህንነት አጀንዳ ተደርጎ የሚቆጠር መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ዘርፉ ቀጥተኛ አካላዊ ጉዳት እና ሰፊ ሀገራዊ ተጽዕኖ ያለው በመሆኑ በኃይል መሰረተ ልማት ላይ የሚያጋጥሙ የሳይበር ጥቃቶች ከሌሎች ተቋማት እንደሚለየው ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሳይበር ደህንነት መመዘኛዎችን ተከተሎ በኃይል ማከፋፈያ እና ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ ደረጃቸውን የጠበቁ የሳይበር ጥቃት መከላከያ ቴክኖሎጂዎች እየተተገበሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል አስተማማኝ ኃይል አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል የሳይበር ስጋቶችን መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
እንደ አቶ ጌትነት ገለፃ በአሁኑ ወቅት ከፕሮጀክቶች ዲዛይን እና ከግዥ ጀምሮ የሳይበር ደህንነት መስፈርቶችን ያሟሉ እንዲሆኑ እንደ ተቋም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው፡፡
የሳይበር ደህንነት ቀጣይነት ያለው ሂደት እንጂ አንድ ቦታ ላይ የሚያቆም ግብ ባለመሆኑ፣ የኢንፎርሜሽን እና የኦፕሬሽን ቴክኖሎጂ ክፍሎችን አስተማማኝነት በማሳደግ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ተቋሙ በሳይበር ደህንነት አጠባበቁ በአፍሪካ ምሳሌ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የተቋሙ ሠራተኞች በሳይበር ደህንነት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የተለያዩ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠናዎች የሚያገኙበትን መተግበሪያ የማልማት ሥራ መከናወኑን የገለፁት አቶ ጌትነት የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል ለአንድ ክፍል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
የሳይበር ደህንነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ23ኛ ጊዜ እንዲሁም በኢትዮጵያ ደግሞ ‹‹ንቁ ዜጋ ደህንነቷ ለተጠበቀ ሀገር›› በሚል መሪ ቃል ለ7ኛ ጊዜ ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2019 ዓ.ም እየተከበረ ይገኛል፡፡