የኒውክሌር ቴክኖሎጂ እያደገ የመጣውን ሀገራዊ የኃይል ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላት ያስችላል

የኒውክሌር ቴክኖሎጂ እያደገ የመጣውን ሀገራዊ የኃይል ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላት ያስችላል

የኒውክሌር ቴክኖሎጂ እያደገ የመጣውን ሀገራዊ የኃይል ፍላጎት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት አስተማማኝ እና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለዲጂታል መሠረተ ልማት እና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ከፍተኛ ሚና አለው።

በመሆኑም እንደ ሀገር የኃይል አስተማማኝነትን ለማረጋገጥ 2 ሺህ 400 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ሁለት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ዩኒቶችን ለመገንባት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱን አብራርተዋል።

ለማመንጫ ግንባታው በባለሙያዎች ከተጠኑ ከ30 በላይ ቦታዎች መካከል ሦስት ቦታዎች መለየታቸውንም ተናግረዋል።

እነዚህ የተለዩ ቦታዎች በዓለም አቀፍ ተቋማት አዋጭነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ቴክኖሎጂውን ከሚያቀርቡ አካላት ጋር ሥምምነት በመፈጸምና የሰው ኃይል በማዘጋጀት ወደ ግንባታ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የማመንጫ ግንባታውን ለማጠናቀቅ እስከ አስር ዓመት እንደሚፈጅ ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደ ሌሎች የኃይል አማራጮች በወቅቶች መፈራረቅ የማመንጨት አቅሙ የማይዋዥቅ በመሆኑ ግንባታው ሲጠናቀቅ ዓመቱን ሙሉ ወጥ በሆነ አቅም በሚያመርተው የኃይል መጠን ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደሚበልጥ ገልጸዋል።

የኒውክሌር ኢንቨስትመንት የመጀመሪያ ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም አንዴ ከተገነባ እስከ 100 ዓመታት የሚዘልቅ እና ለትውልድ የሚተርፍ ትሩፋት ያለው ፕሮጀክት መሆኑን አብራርተዋል።

የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት በማረጋገጥ ኢትዮጵያ በኃይል ምርት ራሷን ከመቻል አልፋ ለውጭ ገበያ በመሸጥ እና ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን በመሳብ ኢኮኖሚያዊ አቅሟን ለማሳደግ የኒውክሌር ኢነርጂ ልማቱ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

Scroll to Top