የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እየተገነባ ይገኛል። የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም ከ77 በመቶ በላይ ደርሷል። ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ለሀገራችን የኃይል አቅርቦት፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ምን ፋይዳ ይኖረዋል?
📌 የኮይሻ ፕሮጀክት የት እንደሚገኝ፣ ስለ ግንባታ ሂደቱ፣ ስለ ኃይል ማመንጨት አቅሙና ለሀገራዊ ልማት ስለሚኖረው አስተዋጽኦ በዚህ ጽሑፍ በወፍ በረር እናስቃኛችኋለን፡፡
👇 የኮይሻን የልማት ታሪክ አብረን እንቃኝ!
የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞንን በሚያዋስነው በኦሞ ወንዝ ታችኛው ተፋሰስ ከአዲስ አበባ በጅማ መስመር በ 540 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። እንዲሁም ከጊቤ ሦስት የውሃ ኃይል ማመንጫ በ 129 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
ተፈጥሮና የሰው ልጅ የምህንድስና ጥበብ ተጋብተው አዲስ የልማት ታሪክ እየፃፈ የሚገኘው የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል ግዙፉ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ታላቅ ፕሮጀክት የሀገሪቱን የኢነርጂ ፍላጎት ከመደገፍ ባሻገር ለዘመናት ተደብቀው የኖሩ ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን በማውጣትና ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘላቂ ሁለንተናዊ ዕድገት በማምጣት ረገድ ተስፋ የተጣለበት የብርሃን ፕሮጀክት ነው፡፡
የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 1,800 ሜጋዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የኮንክሪት ሙሌት ሥራው ከ 81 በመቶ በላይ ሲጠናቀቅ አጠቃላይ የግንባታ አፈፃፀሙ ከ 77 በመቶ በላይ ደርሷል።
ፕሮጀክቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለወጠነቻቸው የልማት ግቦች አስተማማኝና ንፁህ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና በሚጫወተው የኃይል ዘርፍ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ የውጭ ንግድ ማዕከል ለመሆን ያላትን ታላቅ ራዕይ የሚያግዝ ሲሆን በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ቶን የሚደርስ የካርበን ልቀትን በመቆጣጠር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
የዚህን ታላቅ ፕሮጀክት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች እንዲሁም በአካባቢው ማህበረሰብ ህይወት ላይ ያመጣውን ዘላቂ ለውጥ በክፍል ሁለት ይዘንላችሁ እንመለሳለን። አብራችሁን ቆዩ!

