በቤታችን፣ በሥራ ቦታችን ወይም በፋብሪካዎች ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል በድንገት የሚቋረጥባቸውን ምክንያቶች አስበን እናውቃለን? እንግዲያውስ ኤሌክትሪክ ሊቋረጥ የሚችልባቸውን ዋናዋና ምክንያቶች እንንገርዎ፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በተለያዩ ቴክኒካዊና በሌሎች ውጫዊ ምክንያቶች ሊቋረጥ ይችላል።
🔌 የኃይል መቋረጥ ዋና ዋና ምክንያቶች፦
1. የቴክኒክ ብልሽት
በትራንስፎርመሮች፣ በሰርኪዩት መቆጣጠሪያዎችና በኤሌክትሪክ ገመዶች እንዲሁም በኤሌክትሪክ ቁሶች ላይ በሚያጋጥም ብልሽት ኃይል ሊቋረጥ ይችላል፡፡
2. የማስተላለፊያ መስመር ጉዳት
ከኃይል ማመንጫዎች የመነጨውን ኃይል ወደሚፈለገው ማከፋፈያ ጣቢያ በመጓጓዝ ኃይል ወደተጠቃሚው እንዲደርስ የሚያግዙ የከፍተኛ ቮልቴጅ የማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በሚደርስ ብልሽት ወይም ጉዳት ኃይል ሊቋረጥ ይችላል፡፡
3. ከመጠን በላይ የኃይል ጭነት ሲኖር
የኤሌክትሪክ ፍላጎት ከኃይል ኔትወርክና ከመሣሪያዎች ኃይል የመሸከም አቅም በላይ ሲሆን የብልሽት አደጋን በመጨመር የኃይል መቋረጥ ሊያስከትል ይችላል፡፡
4. የታቀዱ የጥገና ሥራዎች
በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የጥገና፣ የጥገና ቅድመ ሥራና የአቅም ማሻሻያ ሥራዎች ሲሰሩ በጊዜያዊነት የኃይል መቋረጥን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
5. ስርቆትና ሆን ተብሎ ማበላሸት
የማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ማማዎች የተወሰኑ ክፍሎች መሰረቅ ወይም መጎዳት የኃይል አቅርቦቱን ሊያስተጓጉል ይችላል።
6. የማመንጨትና የግሪድ ችግሮች
በኃይል ማመንጨት ወይም በግሪድ አሠራር ላይ የሚከሰቱ ችግሮችም የኃይል አቅርቦትን ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ።
7. ሌሎች ውጫዊ ምክንያቶች
ከባድ የአየር ሁኔታ፣ የወደቁ ዛፎችና አደጋዎች በኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ።
⚙️ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ምን ያደርጋል?
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችንና የማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም ለማሻሻልና የኔትወርኩን አስተማማኝነት ለማጠናከር የጥገና፣ የጥገና ቅድመ ሥራና የማዘመን ሥራዎችን ያከናውናል። ብልሽት ሲያጋጥምም ቴክኒካዊ ቡድኖች ምክንያቱን ለይተው ተጎድቶ የነበረውን አገልግሎት ለመመለስ ይሠራሉ።
💡 ኅብረተሰቡስ ምን ማድረግ አለበት?
የተጎዱ ማማዎችን፣ የወደቁ የኤሌክትሪክ መስመሮችንና አጠራጣሪ የሰዎች እንቅስቃሴን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ አለባቸው፡፡
የኃይል መሠረተ ልማቶችን መጠበቅ ለቤተሰብ፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለጤና ተቋማትና ለንግድ ዘርፉ የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት በአግባቡ እንዲደርስ ማድረግ ነው።