ፕሮጀክቶችን ውጤታማ ለማድረግ ከሥራ ተቋራጮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ይገባል

ፕሮጀክቶችን ውጤታማ ለማድረግ ከሥራ ተቋራጮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ይገባል

ከፕሮጀክቶችን የግንባታ እና ጎን ለጎን የሚከናወኑ ሌሎች ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ከሥራ ተቋራጮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከተለያዩ ፕሮጀክቶችና የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተሞክሮና ዕውቀት ለመቅሰም በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከፕሮጀክቱ የሥራ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር መብራቱ ተሾመ በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት የፕሮጀክቱ የስምምነት ውል በፊት ከነበሩ ፕሮጀክቶች የተገኙ ልምዶችን በመጠቀም በመዘጋጀቱ የኮንትራት አስተዳደር ሥራዎች ውጤታማ ናቸው።

በኮንትራት አስተዳደሩ ወቅት የሚኖሩ ተግዳሮቶችን ለመከላከል ብቃት ያለው የህግ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ ገልፀው ፕሮጀክቱ ከዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር አብሮ በመሰራቱ ከኮንትራት አስተዳደር ጋር ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ መቻሉንም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶችን ውጤታማ ለማድረግ ሥራ ተቋራጮችን በአግባቡ መያዝና ግንኙነትቱን ማጠናከር ይገባል ያሉት ኢንጅነር መብራቱ ከፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ ጋር መልካም ግንኙነት ተፈጥሮ በቡድን ስሜት በመሰራቱ የግንባታ፣ የማህበራዊ ኃላፊነትና ሌሎች ሥራዎች ውጤታማ ሆነዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በጋራ መፍትሔ ማስቀመጥና በወቅቱ ውሳኔ መስጠት፣ የተቋሙን የህግ ባለሙያዎች አቅም ማሳደግ፣ በፕሮጀክቶች በተለያዩ ዘርፎች ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን መመደብ እንዲሁም ለአካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ሥራ አስኪያጁ አስገንዝበዋል።

ፕሮጀክቱ ጥራት ባለው መልኩ እንዲገነባ ለማድረግ እያንዳንዱ የኮንክሪት ሥራ ግብዓቶች ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ በላብራቶሪ ተፈትሸውና ጥራታቸው ተረጋግጦ ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ተገልጿል።

የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አብዱልፈታህ በደዊ በበኩላቸው እንደ ሀገር የህግና የመመሪያ ለውጦች ሲስተዋሉ ተቋሙ ላልተፈለገ ወጪ እንዳይዳረግ የህግ ድንጋጌዎችን በአግባቡ ማጤን ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም የህግና ሌሎች ለውጦች ሲኖሩ መፍትሔ የሚሰጥበት አግባብ በፕሮጀክቱ የኮንትራት ስምምነት ላይ መካተታቸውን ጠቁመዋል።

የፕሮጀክት የውጭ ምንዛሬ እስኪገኝ ድረስ በሀገር ውስጥ ገንዘብ የሚሸፈኑ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት ይገባል ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ አሰራሩ በኮይሻ ፕሮጀክት ላይ ተግባራዊ በመደረጉ በአፈፃፀሙ ላይ ውጤት እየተገኘበት ነውም ብለዋ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ እንደተናገሩት በሥራ ተቋራጮች የሚቀርቡ ክፍያዎች በወቅቱ ካልተከፈሉ ተቋሙን ለተጨማሪ ወጪ ስለሚዳርጉ እያንዳንዱን ክፍያዎችና ጥያቄዎች አረጋግጦ በወቅቱ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

ሥራ ተቋራጮች የሥራ አጋር መሆናቸውን ተገንዝቦ መስራት፣ በጣቢያዎች ላይ ተርባይኖችን ከማብዛት ይልቅ ዓመታዊ የኃይል ምርት መጠናቸውን ማሰብ እና በኮንትራት አስተዳደር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም አብራርተዋል።

ተሳታፊዎቹ የፕሮጀክቱን ተሞክሮዎች ሰንዶ ከማስቀመጥ፣ ከማህበራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች፣ ከፕሮጀክት አስተዳደር፣ ፕሮጀክቱ ውጤታማ ስለሆነበትና ተሞክሮዎች ስለሚተገበሩባቸው አግባብ በተመለከተ ጥያቄዎችና ከስተያየቶችን አቅርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

Scroll to Top