የካሳ እና የወሰን ማስከበር ችግሮችን ለመፍታት የጂ.አይ.ኤስ ቴክኖሎጂ ቁልፍ ሚና አለው

የካሳ እና የወሰን ማስከበር ችግሮችን ለመፍታት የጂ.አይ.ኤስ ቴክኖሎጂ ቁልፍ ሚና አለው


የካሳ ክፍያና የወሰን ማስከበር ተግዳሮቶችን በሳይንሳዊ አሰራር በዘላቂነት ለመፍታት የጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሲስተም (GIS) ትልቅ ድርሻ እንዳለው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጀኔሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ አስታወቀ።

ዘርፉ የባለሙያዎችን የጂ.አይ.ኤስ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማጎልበትና በካሳና ወሰን ማስከበር ሥራዎች ላይ አቅም ለመፍጠር ከኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈጻሚ ጋር የጋራ የልምድ ልውውጥ አድርጓል፡፡

በልምድ ልውውጡ ላይ የዘርፉ የወሰን ማስከበርና ካሳ ጉዳዮች ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውዱ ገዛኸኝ እንደገለጹት ቴክኖሎጂው በኃይል ማመንጫዎች፣ ማስተላለፊያ መስመሮች እና ፕሮጀክቶች ላይ ትክክለኛ የካሳ ግምትና የይዞታ መረጃ ለማደራጀት ይረዳል።

አቶ ዘውዱ አክለውም የጂ.አይ.ኤስ አሰራርን መተግበር ግልጽነትና ተጠያቂነትን እንደሚያረጋግጥ ገልጸው ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁና ሀብትን በጥራት ለማስተዳደር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈጻሚ የጂ.አይ.ኤስ ባለሙያ አቶ ታደሰ ጌታቸው በበኩላቸው ቴክኖሎጂው የመሬት መልክአ ምድራዊ መረጃዎችን በመተንተን ወደ ግልጽ ካርታዎችና ግራፎች በመቀየር ፈጣንና ትክክለኛ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል አሰራር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጂ.አይ.ኤስ ቴክኖሎጂን ከካዳስተር መረጃዎች እና ከቀደሙት የፎቶግራፍ መዝገቦች ጋር በማስተሳሰር አወዛጋቢ የሆኑ የካሳ እና የይዞታ ጥያቄዎችን በብቃት ለመፍታት እንደሚያስችል ባለሙያው አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ጂ.አይ.ኤስ የሳተላይት ምስሎችንና ድሮኖችን በመጠቀም የመሬት ለውጦችን ለመከታተል፣ የማመንጫና ማስተላለፊያ ሀብቶችን ለማስተዳደር እና የባለቤትነት መብትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

Scroll to Top