ተቋማዊ ዕውቀት በአግባቡ ተሰንዶ ለቀጣይ ሥራዎች መሸጋገር አለበት — ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ

ተቋማዊ ዕውቀት በአግባቡ ተሰንዶ ለቀጣይ ሥራዎች መሸጋገር አለበት — ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተለያዩ የሥራ ቦታዎች የሚገኙ ዕውቀቶችና ተሞክሮዎች በአግባቡ ተሰብስበውና ተሰንደው ለቀጣይ ትውልድ መተላለፍ እንዳለባቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ አሳሰቡ።

ኢንጂነር ክፍሌ እንደገለጹት፣ ተቋሙ በርካታ ፕሮጀክቶችን ያከናወነና ሰፊ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ያሉት ቢሆንም፣ ከፕሮጀክቶች የሚገኙ ተሞክሮዎችን በሥርዓት የመሰነድ፣ ለሌሎች የማስተላለፍና የተገኙ ዕውቀቶችን ለቀጣይ ሥራዎች የመጠቀም ረገድ ክፍተቶች ይስተዋላሉ።

በመሆኑም ከተለያዩ ሥራዎችና ፕሮጀክቶች የሚገኙ ዕውቀቶች ተሰብስበው፣ ተደራጅተውና ቋት ተይዘው ለቀጣይ ሥራዎች እንዲውሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በተቋሙ የኢትዮ-ፓወር አካዳሚ የተጀመሩ የዕውቀት ማሰባሰብና ማስተላለፍ ሥራዎችም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዕውቀትን መሰነድ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ያስገነዘቡት ኢንጂነር ክፍሌ፣ የተሰነደው ዕውቀት ለሌሎች ባለሙያዎችና ለቀጣይ ፕሮጀክቶች በተግባር እንዲተላለፍ ለማድረግ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ዕውቀትና ተሞክሮን በአግባቡ ማስተላለፍ ተደጋጋሚ ስህተቶችን ለመቀነስ፣ የሥራ ቅልጥፍናን ለማሳደግ፣ ለውጭ ሥልጠናዎች የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስና ተቋማዊ አቅምን በዘላቂነት ለመገንባት እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

በተቋሙ የዕውቀት አስተዳደር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ አለማየሁ በበኩላቸው፣ የዕውቀት አስተዳደርና ሽግግር ሥርዓቱን ለማጠናከር የተለያዩ መመሪያዎችና አሠራሮች መዘጋጀታቸውን እንዲሁም የዕውቀት ዘርፎች መለየታቸውን ገልጸዋል።

የዕውቀት ማሰባሰብ፣ ማደራጀትና ማስተላለፍ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ዲጂታል ፕላትፎርሞችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል። የዕውቀት አስተዳደር ለተቋሙ ካለው ከፍተኛ ፋይዳ አንጻርም ሁሉም የተቋሙ አካላት በሂደቱ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መብራቱ ተሾመ በበኩላቸው፣ በፕሮጀክቱ እስካሁን የተገኙ ዕውቀቶችና ተሞክሮዎች ተሰብስበው መሰነዳቸውን ገልጸዋል። እነዚህንም ለሌሎች ፕሮጀክቶችና ለተቋሙ አካላት ለማስተላለፍ ፕሮጀክቱ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኮይሻ ፕሮጀክትን ተሞክሮዎች ለቀጣይ ሥራዎች ማስተላለፍ የሁሉም የተቋሙ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኮይሻ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልፈታህ በደዊ እንደገለጹት፣ ተቋማዊ አቅምን ለመገንባት በዕውቀት ልየታና ማሰባሰብ ሂደት የሚመለከታቸውን አካላት ማሳተፍ፣ የተገኙ ተሞክሮዎችን በሥርዓት መሰነድና በቀጣይ ፕሮጀክቶች ላይ በተግባር እንዲውሉ ማድረግ ወሳኝ ነው።

Scroll to Top