የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሀገሪቱ ለምታስተናግደው 32ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ (COP-32) ዓለም አቀፍ ጉባዔ የሚፈለገውን አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡
በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ተወካይ ሥራ አስፈጻሚና የኮፕ- 32 ቴክኒካል ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበባው ያለው እንደገለጹት ለጉባዔው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ ከሁሉም የሥራ ዘርፎች የተውጣጣና ሥራዎችን በበላይነት የሚከታተል የቴክኒክ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ተቋሙ ጉባዔው ከሚካሄድበት ቦታና እንግዶች ከሚያርፉባቸው ሆቴሎች እና መዳረሻ ቦታዎችን በማካተት በሁለት ዘርፍ የተከፈሉ 18 ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ጉባዔው በሚካሄድበት ቦታ ያልተቋረጠ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እንዲሁም ባለ 132 እና ባለ 230 ኪሎ ቮልት መጠን ያላቸው ሁለት ተንቀሳቃሽ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ በተቋሙ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አበባው ገለጻ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ እያንዳንዳቸው 50 ሜጋ ቮልት አምፒየር አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች ያሉት ፕሪፋብሪኬትድ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም የኃይል መቋረጥ ቢከሰት ለአራት ሰዓት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል መስጠት የሚችል 15 ሜጋ ዋት አቅም ያለው ዘመናዊ ባትሪ (battery energy storage system) ለመትከል በግዥ ሒደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
እንግዶች ከሚያርፉባቸው ሆቴሎችና ከአዲስ አበባ እስከ 100 ኪሎ ሜትር ባሉ ከተሞች የኃይል መቆራረጥ እንዳይገጥማቸው የአቅም ማሳደግና የማሻሽያ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
ለዚህም በሱሉልታ፣ በወላይታ ሶዶ እና በሐዋሳ አካባቢዎች የሚገኙ ጣቢያዎችን አቅም ለማሳደግ የአውቶ ትራንስፎርመሮች ተከላ ታቅዶ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ አበባው በነባሩ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ እስከ 100 ኪሎሜትር የሚደርስ ከፍተኛ ኃይል የማስተላለፍ አቅም ያለው ዘመናዊ የኮንዳክተር ገመድ ቅየራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ሁሉንም ሥራዎች እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ ሁለት የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጆችን በመመደብ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡
እነዚህ በኃይል መሰረተ ልማቱ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ለጉባዔው አስተማማኝ ኃይል ከማቅረብ ባለፈ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ግሪድ አቅም የሚያጠናክሩ፣ የኃይል ማስተላለፍ ማነቆዎችን የሚፈቱ እና የተቋሙን ፕሮጀክት አፈጻጸም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።