የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የኤሌክትሪክ  ኃይል መሠረተ ልማት ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የኤሌክትሪክ  ኃይል መሠረተ ልማት ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ።

የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ መርሃ ግብር ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል ተካሂዷል፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተፈራርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትን መጠበቅ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው ብለዋል።

ኢንጂነር አሸብር ባልቻ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ተቋሙ የኢትዮጵያን ዕድገትንና ብልጽግናን ለማረጋገጥ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበ ሲሆን የኃይል መሰረተ ልማቶች ደግሞ የሀገር ሀብቶች በመሆናቸው ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የፌዴራል ፖሊስ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ተቋማት መካከል የነበረውን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር እንደሆነ ጠቅሰው ፌዴራል ፖሊስ ለኃይል መሰረተ ልማት  ደህንነትን ለማስጠበቅ ለከፈለው መስዋዕትነት አመስግነዋል ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው የፌዴራል ፖሊስ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የኃይል መሰረተ ልማቶችን እየጠበቀ ይገኛል ነው ያሉት።

ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር

በተጨማሪም ፌዴራል ፖሊስ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ከስርቆት፣ ከሽብር ተግባራት እና ከሌሎች የደህንነት ስጋቶች ለመጠበቅ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡

ስምምነቱ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ተፈጻሚነቱን እና ቀጣይ ሂደት የሚከታተል ከሁለቱም ተቋማት የተውጣጣ የጋራ የደህንነት ኮሚቴ እንደሚቋቋምም ተገልጿል፡፡

Scroll to Top