ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት ለማጠናቀቅ ነቅቶ መስራት ይገባል

ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት ለማጠናቀቅ ነቅቶ መስራት ይገባል

አስተማማኝ ኃይል ለማመንጨት እና የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በጀት ለማጠናቀቅ ሁሉም የዘርፉ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞችኛ በንቃትና በመተባበር መስራት እንደሚጠበቅባቸውት የጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን አሳሰቡ፡፡

ዘርፉ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን በሥሩ ከሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሲገመግም እንደተናገሩት ከፕሮጀክቱ የተገኙ ተሞክሮዎችንና ያጋጠሙ ችግሮችን ለቀጣይ ፕሮጀክቶች ግብዓት በሚሆን መልኩ አደራጅቶ ማስቀመጥ ይገባል፡፡

የግማሽ ዓመቱ የኦፕሬሽንና የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ሪፖርት፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በዘርፉ የዕቅድና ክትትል ቢሮ ሥራ አስኪያጅ በአቶ ማርችፕ መንግስቴ በዝርዝር ቀርቧል፡፡

በዚህም ኃይል ከማመንጨት እንዲሁም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ዝግጁ ከማድረግና አቅማቸውን ከመጠቀም አንጻር የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን በሪፖርቱ ገልፀዋል፡፡

የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈጻጸምን ለማሻሻል እንዲሁም በግልና በመንግስት አጋርነት የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

ሆኖም ከካሳ ጉዳዮች፣ ከፕሮጀክት ስምምነት ውል ተሳትፎ፣ ከሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ካለፉት ፕሮጀክቶች ልምድ ከመውሰድ እንዲሁም የኃይል ማመንጫዎች በሚገነቡበት ወቅት ኦፕሬሽኑን የሚረከብ ሠራተኛ ከማፍራት አንፃር ክፍተቶች መስተዋላቸውን አብራርተዋል፡፡

የፋይናንስ ችግር፣ የፕሮጀክት ዕቃዎችን ከወደብ በወቅቱ ከማጓጓዝ፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በሚፈለገው መልኩ ያለመሟላት፣ የጣቢያዎች መልሶ ግንባታ ሥራ ወቅቱን ጠብቆ ያለመከናወን እንዲሁም ከተሸከርካሪ እጥረት ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንደሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ላይ ከመንግስትና የግል አጋርነት አተገባበር፣ ከጣቢያዎች የጥገና ሥራ፣ ከቢሮ አደረጃጀት፣ ከተሽከርካሪ አቅርቦት፣ ከሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ጋር በተያያዘ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በሥራ ክፍል የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

የጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን በሰጡት የሥራ መመሪያ ለኃይል ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የኃይል ስብጥሩን የሚያሰፉ ፕሮጀክቶችን ከማከናወን ባለፈ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ጣቢያዎችን ዝግጁነት በማረጋገጥ አቅማቸውን በአግባቡ መጠቀም እና የሚፈለገውን ኃይል እንዲያመነጩ ለማድረግ የመልሶ ግንባታና ማሻሻያ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶች ወደ ኦፕሬሽን ሲሸጋገሩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ወጥ የሆነ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት እና ከፕሮጀክቱ የተገኙ ተሞክሮዎችንና ያጋጠሙ ችግሮችን ለቀጣይ ፕሮጀክቶች ግብዓት በሚሆን መልኩ አደራጅቶ ማስቀመጥ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና ወጭ በማጠናቀቅ ተቋሙ የሚፈልገውን ውጤት ለማምጣት ሁሉም የዘርፉ ሠራተኛና የሥራ መሪ በትብብርና በተናበበ መልኩ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top