የተቋሙን መሠረተ ልማቶች ለመጠበቅ የተገኙ ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን ማጠናከር ያስፈልጋል

የተቋሙን መሠረተ ልማቶች ለመጠበቅ የተገኙ ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን ማጠናከር ያስፈልጋል

በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀመውን ስርቆት በዘላቂነት ለመፍታት የታዩ ተስፋ ሰጪ ጅምሮችና የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋም ደህንነት መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው ከሪጅን ኃላፊዎችና ከመሠረተ ልማት ደህንነት የጥበቃ አባላት ኃላፊዎች ጋር በኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ደህንነት ዙሪያ የተከናወኑ ሥራዎችን አስመልክቶ ሲያካሂድ የቆየውን ግምገማ አጠናቋል።

በግምገማው ላይ በሁሉም የተቋሙ ሪጅኖች የተመደቡ የመሰረተ ልማት ጥበቃ የሥራ ኃላፊዎች ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ባከናወናቸው ሥራዎች ላይ የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ቀርበው ተገምግመዋል።

በምስራቅ አንድ ሪጅን አዲጋላ፣ጭሮና አዋሽ የስጋት ቀጣናዎች መሆናቸው የተለየ ሲሆን ቁርጥራጭ ብረቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የስርቆት ምንጩን ለማግኘት ጥረት መደረጉ ሲገለጽ በደቡብ ምዕራብ ሪጅን ሶኮሩ አካባቢ የስርቆት ስጋቶች እና የወሰን ማስከበር ችግሮች በመኖራቸው የአካባቢው የጸጥታ አካላት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን መሰረተ ልማቶቹን በቅንጅት እንዲጠብቁ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

በሰሜን ምዕራብ ሪጅን ካለው የጸጥታ ሁኔታ አንጻር የመስተዳደር አካላትንና ማህበረሰቡን ወርዶ ለማወያየት አዳጋች ቢሆንም የስጋት ቀጣና በሆኑ መስመሮች ከአካባቢው የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የክትትል ሥራዎችን መስራት እንደተቻለ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በአንዳንድ ሪጅኖች የሚገኙ የመስተዳደር አካላት በጋራ ለመሥራት ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆኑ፣ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ወደ ታች ወርዶ ማህበረሰቡን ለማወያየት አለመቻሉ እና የክትትል ሥራዎችን ለመሥራት የተሽከርካሪ እጥረት ማጋጠሙ፣ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎችና የወሰን ማስከበር ችግሮች በሥራቸው ላይ ጫና መፍጠራቸውን ኃላፊዎቹ ባቀረቡት ሪፖርት አመልክተዋል።

የተቋም ደህንነት መምሪያ ዳይሬከተር አቶ ከሊል ሽፋ በግምገማው ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነትን በማሻሻል እና በየደረጃው ከሚገኙ የፌደራልና የክልል መስተዳድር አካላት እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት በመሥራት በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በግማሽ ዓመቱ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።

መመሪያው በ2018 ግማሽ በጀት ዓመት በሪጅኖች ላይ የሚስተዋሉ የሥጋት ቀጣናዎችን ለይቶ የቅድመ መከላከል ሥራ ላይ በትኩረት ለመሥራት የወሰዳቸው የመፍትሔ አማራጮችም ስርቆትን በመከላከል ረገድ ተስፋ ሰጪ ለውጦች ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የስርቆት የሥጋት ቀጣና በሆኑ አምስት ሪጅኖችና አስራ ሁለት መስመሮች ላይ 1 ሺህ 292 የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎችን በየአካባቢው ከሚገኙ የቀበሌ መስተዳደር አካላት ጋር በመነጋገር በህብረተሰቡ እንዲጠበቁ ማድረግ ተችሏል፡፡
በማህበረሰቡ ከሚጠበቁ የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች መካከል በስድስት ወራት ውስጥ በ29 ታወሮች የሥርቆት ሙከራ መደረጉን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በ28 ታወሮች ላይ የሥርቆት ሙከራ ያደረጉ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውንም አስረድተዋል፡፡

በአንጻሩ በማህበረሰቡ በማይጠበቁ በዘጠኝ ቦታዎች ላይ 20 ታወሮች የስርቆት ሙከራ የተደረገባቸው ሲሆን በሦስት ታዎሮች ላይ ተጠርጣሪዎች እንደተያዙ ገልጸዋል፡፡

በ2018 ግማሽ በጀት ዓመት በ11 የከፍተኛ ኃይል ተሻካሚ ምሰሶዎች ላይ 1 ሺህ 285 የሚሆኑ ብረቶች መሰረቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በ2017 ግማሽ በጀት ዓመት በ43 የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ 46 ሺህ 868 ብረቶች መሰረቃቸውን በማስታወስ የደረሰው ጉዳት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በቀጣይም በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት እንዳይፈጸም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመስራት መሰረተ ልማቶችን በማህበረሰቡ እንዲጠበቁ በማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን እና የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

በተቋሙ የንብረትና ጠቅላላ አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ስመኝ አያሌው በበኩላቸው በተቋሙ ንብረቶች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶችን ለመከላከል ለሥራው የሚያስፈልጉ ሌሎች ሎጂስቲኮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ዘርፋቸው ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ደስታለም ኃይሉ በበኩላቸው በየደረጃው የሚገኙ የመስተዳድር አካላትና የአካባቢው ማህበረሰብ አዳዲስ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች እንዲገነቡላቸው ጥያቄዎችን ከማቅረብ በዘለለ ለተገነቡት መሠረተ ልማቶች ደህንነት ትኩረት እንሲሰጡም ነው የጠየቁት።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top