የኮምቦልቻ ቁጥር 1 ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በአካባቢው ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን የጣቢያው ኃላፊ ተናገሩ፡፡
ኃላፊው አቶ ደምሴ ሣህለማርያም እንደተናገሩት የኮምቦልቻ ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያ ለኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ኃይል ለማቅረብ ታስቦ በ1976 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረ ነው፡፡
ጣቢያው በወቅቱ ከሸዋሮቢት ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ተቀብሎ በሰባት ባለ 15 እና በአንድ ባለ 66 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካው፣ ለኮምቦልቻና ለደሴ ከተሞች ኃይል ሲያቀርብ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው 36 ሜጋ ቮልት አምፒር ኃይል የመሸከም አቅም ባላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን በአካባቢው ከኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በተለያዩ ጊዜያት በተከናወኑለት የአቅም ማሳደግና የማስፋፊያ ሥራዎች የትራንስፎርመሮቹን ኃይል የመሸከም አቅም ወደ 80 ሜጋ ቮልት አምፒር እንዲሁም አጠቃላይ የወጭ መስመሮችን ቁጥር ደግሞ ወደ 12 ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ማከፋፈያ ጣቢያው ከኮምቦልቻ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ተቀብሎ በአስር ባለ 15፣ ሁለት ባለ 66 እና አንድ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች በአካባቢው ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች፣ ለኮምቦልቻ፣ ደሴ ከተሞችና በዙሪያው ለሚገኙ ወረዳዎች እንዲሁም ለአቀስታ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ደምሴ ገለፃ ማከፋፈያ ጣቢያው የአቅም ማሳደግ ሥራ ቢከናወንለትም የኃይል ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ለደንበኞች አስተማማኝ ኃይል ማቅረብ እና ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፡፡
ሆኖም በቅርቡ በኮምቦልቻ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ በተደረገ የአቅም ማሳደግ ሥራ የተወሰኑ ደንበኞችን ወደ ቁጥር 2 በማዛወር በጣቢያው ላይ የነበረውን የኃይል ጭነት ማቃለል መቻሉን ጠቁመው በዚህም በሙሉ አቅሙ ይሸከም ከነበረበት 76 ሜጋ ዋት የኃይል ጭነት ወጥቶ አሁን ላይ 24 ሜጋ ዋት የሚጠጋ ትርፍ ኃይል ለማግኘት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ከህዳር 2018 ዓ.ም ጀምሮ የተደረገው ደንበኛ የማዛወር ሥራ የጣቢያውን የፈረቃ የኃይል አቅርቦት ከማስቀረቱም ባለፈ ትራንስፎርመሮች በኃይል መጨናነቅ ምክንያት ከሲስተም ይወጡበት የነበረውን ጊዜ ለማስቀረት እና ተጨማሪ የኃይል ፍላጎት ጥያቄዎችን ለመመለስ ዕድል እንደሚፈጥር ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡
በኮምቦልቻ ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያ የጥገና ባለሙያው አቶ ሰይድ ነጋ በበኩላቸው ጣቢያው የተጣለበትን ተልዕኮ በመረዳት አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ የፍተሻና የጥገና ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በጣቢያው ላይ የጥገና ባለሙያዎች መመደባቸው ለሚያጋጥሙ ችግሮች በወቅቱ መፍትሔ በመስጠት በደንበኞች ላይ ኃይል ተቋርጦ የሚቆይበትን ጊዜ ለማሳጠር ከማስቻሉም በተጨማሪ ተቋሙን ከአላስፈላጊ ወጭ እንደሚያድነው ተናግረዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



