በሁሉም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የኦፕሬሽን አቅምን ለማሳደግ እና የሥራ ላይ ደህንነት መስፈርቶችን ለማስጠበቅ እንደሚሰራ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ አስታወቀ።
በዘርፉ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን የተመራ የባለሙያዎች ቡድን በአዋሽ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የመስክ ምልከታ አድርጓል።
የመስክ ምልከታው በጣቢያዎቹ ወቅታዊ የኦፕሬሽን አፈፃፀም፣ በማመንጨት ሂደት ላይ በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እና በሌሎች የዘርፉ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት ያለመ ነው።
በዚሁ ወቅት ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን እንደተናገሩት ጣቢያዎቹ በሀገራዊ የኃይል አቅርቦት መረብ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ናቸው።



የአዋሽ 2 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው በየጊዜው የኦፕሬሽን መሳሪያዎቹን አስተማማኝነት ማረጋገጥና የቅድመ ጥገና ሥራዎችን በትኩረት ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ረጅም ዓመት ያገለገሉ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ለግሪድ ሥርዓቱ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን የገለፁት ኢንጂነር ኤፍሬም የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም የግዥ ሂደቶችን ማፋጠን እንደሚገባ አብራርተዋል።
በጣቢያዎቹ ከሥራ ላይ ደህንነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ መዘናጋቶችን የማይታለፉ መሆናቸውንም ነው በአፅዕኖት የተናገሩት።
በጣቢያዎቹ ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን በመለየት በፍጥነት ማስወገድ እንደሚገባም ገልፀዋል።
እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ተቋሙ ከሥራ መሣሪያዎች አቅርቦት እና ምቹ የሥራ ከባቢ ከመፍጠር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ይሰራል።
ጣቢያዎቹ በቴክኒክ፣ በአስተዳደር እና በሥራ ላይ ደህንነት ጉዳዮች ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት ያለመ የተቀናጀ የድርጊት መርሃ ግብር በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ አዘጋጅተው እንዲያቀርቡም መመሪያ ሰጥተዋል።
ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከጣቢያዎቹ ሥራ አስኪያጆች እና የጥገና ባለሙያዎች ጋር በመሆን የተርባይንና የመቆጣጠሪያ ክፍሎችን እንዲሁም የግድቡን የውሃ መግቢያ በሮችን ጎብኝተዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



