የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሀገር አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የጀኔሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን ተናገሩ።
ዘርፉ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀሙን እየገመገመ ይገኛል።
ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር ኤፍሬም በግምገማው ላይ እንዳሉት ዘርፉ ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮና የነደፈውን ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማሳካት ቀደም ሲል በተናጠል ሲሰሩ የነበሩት የኃይል ማመንጫ ግንባታ እና የኦፕሬሽን የሥራ ክፍሎችን በአንድ ላይ በማድረግ የተቋቋመ ነው።

የግምገማ መድረኩ የሥራ መሪውና ሠራተኛው በዘርፉ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢንቨስትመንት እና የከተሞች ዕድገትን ተከትሎ በየዓመቱ የኃይል ፍላጎት እየጨመረ ይገኛል ያሉት ኢንጅነር ኤፍሬም ይህን ፍላጎት ለማሟላትም በኃይል ማመንጨት እና ግንባታ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ አጠቃላይ ኃይል የማመንጨት አቅም 9 ሺ 749 ሜጋ ዋት መድረሱንና ከዚህ ውስጥ 9212 ከውሃ፣ 504 ከነፋስ እንዲሁም ቀሪው ከደረቅ ቆሻሻና ከእንፋሎት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ የባለፋት የ10 ዓመት የኃይል አጠቃቀም በአማካይ የ12 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት እያሳየ በመሆኑ በቀጣይ ሊመጣ የሚችለውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል፡፡
የዘርፉ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ለግምገማ የቀረበ ሲሆን የግማሽ በጀት ዓመቱ ጠንካራና ደካማ ጎኖች፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ተገምግመው ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
