በደሴ ከተማ አካባቢ በግንባታ ላይ የሚገኘው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳደግ ከሌሎች ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን ያስችላታል ሲሉ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተናገሩ፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የደሴ ከተማና አካባቢው የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚያገኙት በከተማዋ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሲሰጥ ከቆየው የ66 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ነው፡፡
ሆኖም ከከተማዋ መስፋፋት እና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ጣቢያው በየጊዜው እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ በአግባቡ እየመለሰ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
በደሴ ከተማና አካባቢው በንግድ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ቢኖሩም የኃይል አቅርቦት ችግሩ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት ተፅዕኖ ከመፍጠሩም ባለፈ የማህበረሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የኃይል ፍላጎት ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ባከናወነው ሥራ አሁን ላይ በደሴ ከተማ አቅራቢያ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ተጀምሮ የግንባታ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የከተማዋን የኃይል አቅርቦት ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሻግረው በመሆኑ የከተማዋ ነዋሪ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እስኪጀምር ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው ወደ ሥራ ሲገባ የአምራች ኢንዱስትሪዉን በማስፋፋት፣ ምርታማነትን በማሳደግ እና የሥራ አጥ ቁጥርን በመቀነስ በአካባቢው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ልማትን በማረጋገጥ ተወዳዳሪ ከተማና ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአካባቢው ያለውን የኃይል አቅርቦት ችግር ተገንዝቦ ፕሮጀክቱን መጀመሩን አመስግነው በተዘለት ጊዜ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም ጠይቀዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ማከፋፈያ ጣቢያው የሚገነባበትን ቦታ ከሦስተኛ ወገን ነፃ ከማድረግ ጀምሮ የግንባታ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል፡፡
በደሴ ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ አለባቸው ሰኢድ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠጥ ሲጀምር በአካባቢው ያለውን የኃይል አቅርቦት ችግር በመቅረፍ የኢንቨስትመንት ፍሰትን እና ምርታማነትን እንደሚያሳድግ ገልፀዋል፡፡


የፕሮጀክቱን መጀመር ተከትሎ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን እያቀረቡ መሆኑንና በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 75 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄ ማቅረባቸውንም ለአብነት አንስተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለሀብቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ እንደሆነ አቶ አለባቸው አስረድተዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


