ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ማዕከል በመሆን የምስራቅ አፍሪካን ቀጣና እያስተሳሰረች መሆኑን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ገለጹ።
በተባበሩት ዐረብ ኢምሬት አቡዳቢ ከጥር 03 እስከ ጥር 04 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ “Powering Humanity: Renewable Energy for Shared Prosperity” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው 16ኛው የዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ (IRENA) ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በመሳተፍ ላይ ትገኛለች።
አምባሳደር ጀማል በጉባኤው ባቀረቡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መግለጫ ሀገሪቱ የምትጠቀመው ኃይል ከ98 በመቶ በላይ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ ታዳሽ ኃይል ማመንጨት ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ የንጹህ ኃይል አከፋፋይ በመሆን ቀጣናውን ማስተሳሰሯን እንዲሁም በነዳጅ የሚሰሩ ተሽካርካሪዎች እንዳይገቡ በማገድ ከዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗን አንስተዋል።
ይህም የኢኮኖሚ ዕድገቷን ከካርቦን ልቀት ነፃ በሆነ መንገድ ለማረጋገጥ ያስቀመጠችውን ግብ ስኬታማነት የሚያሳይና ለሌሎች አዳጊ ሀገራት እንደ ሞዴል የሚወሰድ ተሞክሮ መሆኑን አብራርተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምጽ ሆና እንደምትቀጥል አጽንኦት የሰጡት አምባሳደር ጀማል እ.አ.አ በ2027 በአዲስ አበባ የሚካሄደው 32ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ሀገሪቱ በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ያላትን ግንባር ቀደም ሚና የምታጠናክርበት እንደሚሆን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ጉባዔው ለአዳጊ ሀገራት ፍትኃዊ የኃይል ሽግግር እንዲረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድጋፎች እንዲሳለጡ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።
አምባሳደር ጀማል ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት እና ኩባንያዎች ኃላፊዎች ጋር የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማት የማስፋፊያ ግንባታዎችን እንዲሁም ለኮፕ 32 ጉባኤ ስኬት ድጋፍ ማሰባሰብ ላይ ያተኮሩ ውይይቶችንም አድርገዋል።
ዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ የታዳሽ ኃይል ላይ ትኩረቱን በማድረግ ለሀገራት የቴክኒክ ዕውቀትና የፖሊሲ ምክር የሚሰጥ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ተቋም በመሆን የተመሰረተ ሲሆን ኢትዮጵያ የማቋቋሚያ ስምምነቱን በመፈረም መሥራች አባል መሆኗ ይታወቃል።
የመረጃ ምንጩ EBC ነው
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



