ለለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ኃይል ለማቅረብ እየተከናወነ የሚገኘው የማከፋፊያ ጣቢያ ግንባታ እና የማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲጠናቀቅ የማማከርና የቁጥጥር ሥራዎች በአግባቡ እየተከናወኑ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጂነሪንግ ዘርፍ ገለጸ፡፡
በዘርፉ የፕሮጀክቱ ሬዚደንት ማናጀር አቶ እሸቱ ፋንቱ እንደገለጹት ለፋብሪካው ኃይል ለማቅረብ ተቋሙ ከዲዛይንና ተቋራጭ መረጣ ጀምሮ የማማከር አገልግሎት ለመስጠት ሰኔ 2015 ዓ.ም ተፈራርሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
የማማከር ሥራው ግንባታው በሚካሄድበት ወቅት ኮንትራቱን የማስተዳደርና ፕሮጀክቱ በጸደቀው ዲዛይን መሰረተ እየተከናወነ ስለመሆኑ የመከታተል ሥራዎችን የሚያካትት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ዢያን ኤሌክትሪክ ኢንጅነሪንግ በተባለ የቻይና ሥራ ተቋራጭ እየተከናወነ መሆኑን አቶ እሸቱ ጠቁመዋል።
የግንባታ ሥራው የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማሟላት ያለባቸውን ስታንዳርድና ጥራት ጠብቆ እንዲከናወን ተቋሙ አስፈላጊውን ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ ለሲሚንቶ ፋብሪካዉ ኃይል ለማቅረብ ከደብረ ብርሃን ለሚ 76 ነጥብ 28 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነጠላ ሰርኪዩት ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በመሰመሩ ላይ 190 የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ ምሰሶዎች እንደሚኖሩ የተናገሩት ኃላፊው ከእነዚህ ውስጥ የ186ዎቹ ተከላ መጠናቀቁን እና የመስመር ዝርጋታውም ከ30 በመቶ በላይ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ውስጥ የሚገነባው የማከፋፊያ ጣቢያ 200 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም የሚኖረው ሲሆን አሁን ላይ የሲቪል ስራው 97 ከመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በውጭ ምንዛሪ መተማመኛ ወይም ሌተር ኦፍ ክሬዲት መዘግየት የተነሳ ከታቀደለት ጊዜ አንጻር የተወሰነ መዘግየት ማጋጠሙን አቶ እሸቱ ተናግረዋል።
አሁን ላይ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አማካይ አፈጻጸም ከ70 በመቶ በላይ መድረሱን እና ቀሪ ሥራዎችን በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተቋሙ የሲቪል ሥራዎች ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አቶ ዳንኤል ጸጋዬ በበኩላቸው ለፋብሪካው አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ በደብረ ብርሃን ማከፋፊያ ጣቢያ ላይ የወጪ መስመር የማስፋፊያ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የማስፋፊያው የሲቪል ሥራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ፋብሪካው ሲጠናቀቅ ለሀገር የሚሰጠውን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተቋሙ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ኃላፊዎቹ ገልፀዋል።
የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ኢኩፒሜንት ኢንስታሌሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አረጋዊ ኃይለማርያም እንደተናገሩት ደግሞበ ፋብሪካው ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር በኢትዮጵያ ያለውን የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ይቀርፋል።
የሀገሪቱን 50 በመቶ የሲሚንቶ ፍላጎት እንደሚሸፍን ለሚጠበቀው ለሲሚንቶ ፋብሪካው የኃይል አቅርቦት መሰረታዊ ነገር በመሆኑ ፋብሪካቸው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በቅንጅት እየሰራ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
ፋብሪካው ከተቋሙ ጋር በመጀመሪያው ምዕራፍ መቶ ሜጋ ዋት እንዲሁም በሁለተኛው የማስፋፊያ ምዕራፍ ተጨማሪ መቶ ሜጋ ዋት ኃይል ማግኘት የሚያስችለውን ሥምምነት ተፈራርሞ ወደ ሥራ መግባቱን አቶ አረጋዊ ተናግረዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
ሐምሌ 08 ቀን 2016 ዓ.ም