የወላይታ ዞን አስተዳደር፣ የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የሴኔት አባላትና የፓወር ኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፍ መምህራን የጊቤ 3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ጎበኙ።
ጉብኝቱ የተካሔደው የጣቢያው ሠራተኞች በዩኒቨርስቲው የኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት በተከታታይ የትምህርት መርሀ-ግብር ፕሮግራም በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ (ፓወር ስትሪም) ለ5 ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለው በተመረቁበት ወቅት ነው።
በመስክ ጉብኝቱ ወቅት ገለፃ ያደረጉት የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ሰሙ እንደገለፁት የኃይል ማመንጫው በማመንጨት አቅሙ አሁን በሥራ ላይ ካሉት መካከል ከፍተኛ ሲሆን የታላቁ ኤትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የሁለተኛነት ደረጃ የሚይዝ ነው።
ሥራ አስኪያጁ የኃይል ማመንጫው ስለሚያከናውናቸው የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች፣ የግድብ ደህንነት ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የኃይል ማምረት ሂደት ለጎብኚዎቹ ገለፃ አድርገዋል።
የወላይታ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘካሪያስ ታደሰ ከጉብኝቱ በኋላ እንደተናገሩት ዞኑ በተፈጥሮ የታደለ አካባቢ በመሆኑ የኃይል ማመንጫው የዚህ ትሩፋት ውጤት ነው።
የጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ በመሆኑ የዞኑ አስተዳደር በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተለው ገልፀዋል።
ዞኑ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር ለኢትዮጵያ መሰረተልማቶች መጠበቅ ሁሉን አቀፍ እገዛ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም ነው ኃላፊው የጠቀሱት።
በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀመውን የስርቆት ወንጀል ለመከላከል የዞኑ የፀጥታና ፍትህ አካላት በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የዋቻሞ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ፣ ምርምርና ማህበረሰብ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታምራት ታገሰ በበኩላቸው በጊቤ ተፋሰስ ላይ የሚገኙት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በፓወር ኢንጅነሪንግ የምርምር ዘርፍ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ዩኒቨርስቲው “ብርሃናችሁ በማህበረሰቡ ውስጥ ይብራ!” የሚለውን መሪ ቃል ተግባራዊ ለማድረግ ለማህበረሰቡና ለተቋማት ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን በማከናወን ጉልህ ድርሻ የሚሰጣቸው ውጤቶች ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
ዩኒቨርስቲው የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዶ/ር ታምራት በጊቤ 1፣ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እየተማሩና እየተመረቁ የሚገኙ ሠራተኞች ለዚህ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጅነሪንግ የትምህርት መስክ የተመረቁት የጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሠራተኞች የሀገር ጀግኖች ናቸው ሲሉም ነው ያወደሱት።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”