የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ተማሪዎችን አስመረቀ

የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ተማሪዎችን አስመረቀ

የጊቤ-3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን 27 ወንድ እና 2 ሴት ሠራተኞች በቅድመ ምረቃ ፕሮግራም በማመንጫ ጣቢያው ግቢ ውስጥ አስመርቋል።

በዛሬው ዕለት የተመረቁት የጣቢያው ሠራተኞች በዩኒቨርስቲው የኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት በተከታታይ የትምህርት መርሀ-ግብር ፕሮግራም በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ( ፓወር ስትሪም) ለ5 ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስላለፉት የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሃብታሙ አበበ ዩኒቨርስቲው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የማህበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ፣ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ንቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን እያፈራ ይገኛል።

ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የትምህርት መስኮችን በመቅረፅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ በጊቤ 1፣ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እየተማሩና እየተመረቁ የሚገኙ ሠራተኞች ለዚህ ማሳያ ናቸው ብለዋል።

እንደ ዶ/ር ሃብታሙ ገለፃ ዩኒቨርስቲው በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ እያከናወናቸው በሚገኙ የመማር ማስተማር ሒደቶች ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያልተቋረጠ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን ሲያደርግ በመቆየቱ ምስጋና ይገባዋል።

በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁት ተማሪዎች በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት የተሰጠውን የመውጫ ፈተና ሙሉ በሙሉ ማለፍ መቻላቸውንም ነው የገለፁት።

በዩኒቨርቲው የፖወር ኢንጅነሪንግ የትምህርት መስክ እንዲከፈት መሠረት የጣሉትና በጊቤ 3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ትምህርቱ እንዲሰጥ የዩኒቨርስቲውን ሴኔት ያሳመኑትን የቀድሞው የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕረዚዳንት ዶ/ር አሻሞ ኤራንቆን አመስግነዋል።

የወላይታ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘካሪያስ ታደሰ እንደተናገሩት ትምህርት ስብዕናው የተገነባ ስራ ፈጣሪ ዜጋ በመቅረፅ ረገድ የሚጫወተው ሚና ጉልህ ስፍራ ይሰጠዋል።

መንግሥት ለፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት መጎልበት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ዩኒቨርስቲዎች በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የበኩላቸውን እየወተጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት የአስተዳደራዊ ጉዳዮችና ዶክመንቴሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ በበኩላቸው ተቋሙ በሰው ኃይል ግንባታ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ መሆኑን የዛሬ ተመራቂዎች ማሳያ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትምህርትና ሥልጠና፣ በምርምር ዘርፍ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረታቸውን ባደረጉ መስኮች ላይ በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ለዓመታት የጊቤ-1፣ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሠራተኞችን በፖወር ኢንጅነሪንግ የትምህርት መስክ እያስተማረ በማስመረቅ ላይ በመሆኑ በተቋሙ ስም ምስጋና እንደሚገባው ተናግረዋል።

ከትምህርት ክፍሉና ከዩኒቨርሲቲው 3 ነጥብ 98 በማምጣት የላቀ ውጤት ያስመዘገበው የተቋሙ ሠራተኛ ታሪኩ ጠንክር የወርቅ ሜዳሊያ እና የምስክር ወረቀት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት እጅ ተሸልሟል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጊቤ-3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ ሰሙን ጨምሮ የጣቢያው ሠራተኞች፣ የዋቻሞ ዩኒቨርስቲ የሴኔት አባላትና የትምህርት ዘርፉ መምህራን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top