በትምህርት ላይ ያገኙትን ዕውቀት በሥራ ላይ ለማዋል እንደሚተጉ ተመራቂዎች ገለፁ

በትምህርት ላይ ያገኙትን ዕውቀት በሥራ ላይ ለማዋል እንደሚተጉ ተመራቂዎች ገለፁ

የጊቤ-3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን 27 ወንድ እና 2 ሴት ሠራተኞች በቅድመ ምረቃ ፕሮግራም በማመንጫ ጣቢያው ግቢ ውስጥ አስመርቋል።

ከተመራቂዎች መካከል በጣቢያው የኦፕሬሽን ክፍል ተወካይ ኃላፊ የሆነው ታሪኩ ጠንክር እንደገለፀው ላለፉት 5 ዓመታት ከሥራ ጎን ለጎን ትምህርቱን በትጋት ሲከታተል መቆየቱን ተናግሯል፡፡

በዚህም 3 ነጥብ 98 በማምጣት ከትምህርት ክፍሉና ከዩኒቨርሲቲው የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎ የወርቅ ሜዳሊያ እና የምስክር ወረቀት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት እጅ ተሸልሟል።

በኃይል ማመንጫ ጣቢያው የመካከለኛ ክሊኒክ የህክምና ባለሙያ የሆነው ሔኖክ ተካልኝ እንደተናገረው በዋቻሞ ዩኒቨርስቲ በተከታታይ የትምህርት መርሀ-ግብር ፕሮግራም በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ (ፓወር ስትሪም) ለ5 ዓመታት ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡

በጣቢያው ውስጥ የህክምና ባለሙያ ብሆንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ያመቻቹትን ዕድል በመጠቀም ለዚህ ክብር በቅቻለሁ ብሏል፡፡

ሔኖክ 3 ነጥብ 89 በማምጣት ከትምህርት ክፍሉና ከዩኒቨርሲቲው የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎ በከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ሜዳሊያ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት እጅ ለመሸለም በቅቷል፡፡

በዕለቱ ከተመረቁ የጣቢያው ሴት ሠራተኞች መካከል የሆነችው ብርቱካን አቢ እንደገለፀችው ባለፉት 5 ዓመታት በንድፈ ሃሳብ የቀሰመችውን ዕውቀት በስራ ላይ በማዋል የኃይል ማመንጫውን የጥገናና የኦፕሬሽን ሥራ ለማቀላጠፍ እንደሚረዳት ተናግራለች፡፡

በጣቢያው በቆችባቸው 10 ዓመታት ያገኘቻቸው ልምዶች ለትምህርቷ አጋዥ እንደሆኑላትም ነው የጠቀሰችው፡፡
ብርቱካን 3 ነጥብ 21 ውጤት መስመዝገቧን ተከትሎ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት እጅ የወርቅ ሜዳሊያ ለመሸለም በቅታለች፡፡

ተመራቂዎቹ በዩኒቨርስቲው የፖወር ኢንጅነሪንግ የትምህርት መስክ እንዲከፈት መሠረት የጣሉትና በጊቤ 3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ትምህርቱ እንዲሰጥ የዩኒቨርስቲውን ሴኔት ያሳመኑትን የቀድሞው የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕረዚዳንት ዶ/ር አሻሞ ኤራንቆን እና መምህራኖቻቸውን እንዲሁም የኢትዮጵያ አሌክትሪክ ኃይልን አመስግነዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top