የቢሾፍቱ ቁጥር 3 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በቀን እስከ 80 ሜጋ ዋት ኃይል ጭነት እየተሸከመ መሆኑን የጣቢያው ኃላፊ አስታወቁ።
ኃላፊው አቶ ሲሳይ አይቸው እንደተናገሩት ጣቢያው በአቅራቢያው ለሚገኙ ፋብሪካዎች፣ ለቢሾፍቱ፣ ለዱከም እና ሞጆ ከተሞች በቀን እስከ 50 ሜጋ ዋት በማቅረብ ላይ ይገኛል።
ቀሪውን 30 ሜጋ ዋት ደግሞ በዳታ ማይኒንግ ለተሰማራ የውጭ ኩባንያዎች በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እያመነጨ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ጣቢያው የኃይል ስርጭቱን የሚያሳልጡ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ሁለት ባለ 600 ሜጋ ቮልት አምፒር እንዲሁም አራት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች ያሉት መሆኑንም ነው አቶ ሲሳይ የገለፁት።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ የጣቢያው ስድስት የኃይል ትራንስፎርመሮች እያንዳንዳቸው የእሳት መከላከያ መሳሪያ የተገጠመላቸው መሆኑ ጣቢያውን ከሌሎች የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለየት ያደርገዋል።
በማከፋፈያ ጣቢያው የተገነቡት ደረጃቸውን የጠበቁ የሠራተኛ መኖሪያ ቤቶች ምቹ የሥራ አካባቢ በመፍጠር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
የቢሾፍቱ ቁጥር 3 ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በ2012 ዓ.ም በይፋ ተመርቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



