የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአካባቢያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ሥራዎች ማከናወኑን የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።
ምክትል ሥራ አስኪያጁ ኢንጂነር አባይነህ ጌትነት እንደገለፁት የፕሮጀክቱ ግንባታ በአካባቢ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሊፈጥራቸው የሚችሉ አወንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ጥናት ተደርጎባቸዋል።
ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን የአካባቢና ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚያስችሉ በርካታ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በፕሮጀክቱ አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ የእኔነት ስሜት እንዲኖረው ለማድረግ 30 በመቶ የሥራ ዕድል መመቻቸቱንም ነው ኢንጂነሩ የገለፁት።
የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የአካባቢና ማህበራዊ ጉዳዮች ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ደሳለኝ በበኩላቸው አካባቢው በርካታ የመሠረተ ልማት ችግሮች እንደነበሩበት አንስተዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ግድቡ በሚያመጣው አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ዙሪያ ውይይቶች መደረጋቸውንም ነው የጠቀሱት።
ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ከ85 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድና በኦሞ ወንዝ ላይ 175 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይ መስራቱን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።
የድልድዩ መገንባት በኦሞ ወንዝ ምክንያት ተራርቀው የቆዩ አጎራባች ወረዳዎችን ከማቀራረቡም በላይ የገበያ ትስስር በመፍጠር የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር በር መክፈቱን ገልፀዋል።
በፕሮጀክቱ የተገነቡት የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የጀነሬተር አቅርቦት እንዲሁም የቤተ-እምነት ግንባታዎች ፕሮጀክቱ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ቅቡልነቱ እንዲያድግ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ግዛቸው ገለፃ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በላይኛውና ታችኛው የኦሞ ተፋሰስ ላይ እየተከሰቱ የሚገኙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት እያከናወነ ነው።
ይሁን እንጂ ለሚደርሱ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ምላሽ ለመስጠት የተቋሙ አቅም ውስን በመሆኑ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አስተዳደሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚጠይቅ ነው ሥራ አስኪያጁ ያመለከቱት።


